በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፍሪካ ቀንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ - የተመድ ድርጅቶች


በአፍሪካ ቀንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ - የተመድ ድርጅቶች
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:16 0:00

በአፍሪካ ቀንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉ - የተመድ ድርጅቶች

የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭትን ጨምሮ በተደራራቢ አደጋዎች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአፍሪካ ቀንድ ነዋሪዎች በአስቸኳይ የረሃብ አደጋ እና የጤና ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ገለጹ።

በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና የሚገኙ ሰባት ሀገራት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ የምግብ ዋስትና እጦት ውስጥ መሆናቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል። ስልሳ ሚሊዮን የሚሆን ህዝብም ንቁ እና ጤናማ ሆነው ለመቆየት የሚያስፈልገውን በቂ ምግብ እንደማያገኙም ባወጣው ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

የተቋሙ ከፍተኛ የአደጋ ጊዜ ኃላፊ ዶምኒክ ፌሬቲ፣ የረሃብ ቀውሱ የተመጣጠነ ምግብ እጦት እንዲጨምር ማድረጉን ገልፀው፣ በአፍሪካ ቀንድ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ ሕፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አስታውቀዋል። ከነዚህ፣ የከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ካለባቸው ህፃናት መካከልም 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ልዩ የምግብ ድጋፍ ካላገኙ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

"ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ ምስራቅ አፍሪካ ኮቪድ 19፣ የኢቦላ ወረርሽኝ እና ሌሎች እንደ ኮሌራ እና ኩፍኝ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን እንዲሁም ደንጊ የተሰኘውና በትንኝ አማካኝነት የሚተላለፈው በሽታ አስተናግዷል። የበረሀ አንበጣ ወረርሽኝም በአካባቢው የሚገኘውን ሰብሎች እና መተዳደሪያ አውድሟል" ያሉት ፌሬቲ፣ "ከሁሉ የከፋው ደግሞ በቀጠናው ያለው ሰፊ ግጭት እና አለመረጋጋት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እና እንደ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና አለመታደል ሆኖ ሱዳንም አዳዲስ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች እንዲፈጠሩ ማድረጉ ነው" ሲሉ እነዚህ አስደንጋጭ አኃዞች በአንድ ድንገተኛ አደጋ ብቻ የተከሰቱ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።

በአፍሪካ ቀንድ መጣል የጀመረው ዝናብ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ረጅም ጊዜን ላስቆጠረው የድርቅ አደጋ እፎይታን ቢያስገኝም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ግን ዝናብ ብቻውን ቀውሱን ለማስቆም በቂ እንዳልሆነ እያስጠነቀቁ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት፣ የአፍሪካ ቀንድ የሚኖሩ ሰዎች ከፍተኛ የጤና አደጋዎችን እየተጋፈጡ መሆኑን ያመለክታል። በጤና ተቋሙ የአስቸኳይ አደጋ ዋና ኃላፊ የሆኑት ሊዝቤት አልብሬችት እንደሚያስረዱት፣ አምስት አመታትን በዘለቀው ድርቅ ሳቢያ በርካታ የጤና ችግሮች ተከስተዋል።

"በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ፣ ባለፈው አመት እና በዚህ አመት እንደ ኮሌራ እና ኩፍኝ የመሳሰሉ ወረርሽኞችን እያየን ነው። ቁጥር በጣም ከፍተኛ የሆነ የወባ በሽታም አለ። ስለዚህ በጎርፍ ተፅእኖ ምክንያት እነዚህ በሽታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ እያየን ነው" ሲሉም፣ በከፍተኛ ዝናብ እና ከባድ የጎርፍ አደጋዎች በተጎዱ አካባቢዎች የጤና ችግር እየተባባሰ እንደሚሄድ አስጠንቅቀዋል።

በምዕራቡ የአፍሪካ ቀንድ ክፍል ከድርቁ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ሁኔታ በቀጠለበት ወቅት፣ በምስራቁ አካባቢ ተጨማሪ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑ፣ የዓለም ጤና ድርጅት አዳዲስ ፈተናዎችን እንዲጋፈጥ እያደረገው መሆኑን አልብሬችት ጨምረው ገልፀዋል። ሁለቱም ከባድ የአየር ሁኔታ ክስተቶች የንጹህ ውሃ አቅርቦትን እንደሚቀንሱም አስረድተዋል። አልብሬችት አክለውም፣ ይህ ሁኔታ የወባ እና ሌሎች ውሃ ውለድ በሽታዎች እንዲስፋፉ እንደሚያደርግና በሰዎች የአመጋገብ እና የጤና ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድርም አክለው ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG