ቻይና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ የከፈተችው የቁጥጥር ዘመቻ ፈጠረው ሥጋት እና ዋናዋ የቴክኖሎጂ መናኸሪያዋ ሼንዜን በመዘጋቷ የቴክኖሎጂ ኩባኒያ በመጎዳታቸው ዛሬ የሆንግ ኮንግ የቴክኖሎጂ አክስዮን ዋጋ በአራት ከመቶ መቀነሱ ተዘገበ።
ቀውሱ የሆንግ ኮንግን ኢንቬስተሮች አደናግጧል። በዚህም ላይ ቻይና በሀገሯ ዙሪያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎ አስራ ሰባት ሚሊዮን ነዋሪ ያላትን ሼንዜን ከተማን መዝጋቷም ስጋቱን አባብሶታል። እስከሳምንቱ መጨረሻ ድረስ ነዋሪዎች ከቤት እንዳይወጡ ታዘዋል። የህዝብ ማመላለሻዎችም ተዘግተዋል። ከዚሁ ተያይዞ በከተማዋ የአይፎን ስልክ አምራቹ አፕል ኩባኒያ ዋና አቅራቢ ፎክስኮን እንቅስቃሴውን አቋርጧል።
የታይዋኑ ሆን ሃይ ኩባንያም በከተማይቱ ያለውን ፋብሪካውን ለምን ያህል ጊዜ ዘግቶ እንደሚያቆይ ባይገልጽም የምርት ሥራውን ወደሌሎች አካባቢዎች አዛውሯል።
የአክዮን ዋጋው ያሽቆለቆለው ሩስያ በዩክሬይን ላይ የከፈተችው ወረራ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀሰቀሰው ሥጋት ሳቢያ መሆንም ተመልክቷል። በወረራው ምክንያት የነዳጅ ዋጋ እጅግ ያሻቀበ ሲሆን ቀድሞውንም ጨምሮ የነበረውን የዋጋ ንረት ያባብሰዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ቀደም ሲል ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን የተባለው የዩናይትድ ስቴትስ የገበያ ህግ አስከባሪው ተቋም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተመዘገቡ አምስት የቻይና ኩባኒያዎችን የተሰጣቸውን የኦዲት ምርመራ ደንብ እንዲያከብሩ አለዚያ ከዎል ስትሪት እንደሚታገዱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል።