በቅርቡ በቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተደረገውን የግድያ ሙከራ የሚመረምር ገለልተኛ ቡድን መሰየማቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚንስትር አስታወቁ። ሚንስትር አሌሃንድሮ ማዮርካስ አያይዘውም የሰየሙት ገምጋሚ ቡድን ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።
ጉዳዩን አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት አስተያየት የሰነዘሩ ተንታኞች በበኩላቸው፣ “የቡድን አባላት የፕሬዝደንታዊ ጥበቃ ክፍሉም ሆነ ሌሎች የሕግ አስከባሪ ተቋማት ለቀድሞው ፕሬዝደንት የምርጫ ዘመቻ ተገቢ ጥበቃ ለማድረግ የነበራቸውን ዝግጅት እና የወሰዷቸውን እርምጃዎች ለመገምገም የሚያስችል ከሕግ ማስከበር እና ከጸጥታ ጉዳዮች ጋራ የተዛመደ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል’ ብለዋል።
ቡድኑ ቅዳሜ ሐምሌ 6 ቀን 2016ዓም በትለር ፔንስልቬንያ ውስጥ ትራምፕ የምረጡኝ ዘመቻቸውን እያካሄዱ ሳሉ የግድያ ሙከራ በተደረገባቸው ወቅት እና ከዚያ አስቀድሞም ሆነ በኋላ በነበሩት ጊዜያት የፕሬዝዳንታዊው ጥበቃ አገልግሎት ክፍል የተከተላቸውን እና ተግባር ላይ ያዋላቸውን የአሰራር ደምቦች እና ሂደቶች ለመገምገም የ45 ቀናት ዕድሜ እንደሚኖረው ተመልክቷል።
የፕሬዝደንታዊ ጥበቃ አገልግሎት ክፍሉ ድሬክተር ኪም ቺትል በበኩላቸው የክፍላቸው ሥራ እንዲገመገም የተላለፈውን ውሳኔ በደስታ የሚቀበሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም