ማክሰኞ ዕለት ፕሬዚዳንታቸውን የመረጡት አሜሪካዊያን ረጅም ጊዜ ከፈጀውና መከፋፈልን ከፈጠረው የምርጫ ሂደት በፍጥነት በማገገም ለቀጣዩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እድል እንዲሰጡና አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩ የሀገሪቱ መሪዎች እየወተወቱ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትረምፕ ፕሬዚዳንትነት ሆነው መመረጥ አልዋጥ ያላቸው በሽሕዎች የተቆጠሩ አሜሪካዊያን የተቃውሞ ሠላማዊ ሰልፎች አካሂደዋል።
በትናንትናው ዕለት የዶናልድ ትረምፕን አሸናፊነት በህዝብ ፊት አምነው የተቀበሉት የዴሞክራቶቹ ዕጩ ሂላሪ ክሊንተን የሃሳብ ልዩነቶች ቢኖርም ደጋፊዎቻቸው ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ዕድል እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
“ሀገራችን የገባችበትን ጥልቅ መከፋፈል አስተውላችኋል? አሁንም ግን በአሜሪካ እምነት አለኝ፡፡ ሁልጊዜም ይኖረኛል፡፡ እናንተም ተመሣሣይ አስተሳሰብ ካላችሁ ውጤቱን ተቀብላችሁ የወደፊቱን አስተውሉ፡፡ ዶናልድ ትረምፕ ፕሬዚደንታችን ይሆናሉ፡፡ የመሪነት ዕድል እንዲያገኙ መፍቀድና አይኖቻችንን ገልጠን የሚሠሩትን መመርመር ይገባናል እላለሁ፡፡” ብለዋል ሚስ ክሊንተን በንግግራቸው፡፡
የቪኦኤ ዘጋቢዎች ከኒውዮርክና ዋሽንግተን ዲሲ ያስተላለፏቸውን ዘገባዎች ሔኖክ ሰማእግዜር ያቀርበዋል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡