ህንድ ለብሪክስ አባል ሀገራት የጋራ መገበያያ ገንዘብ የመፍጠርን ሐሳብ እንደማትደግፍ ኒው ዲልሂ የሚገኙ ተንታኞች ተናገሩ፡፡ ዘጠኝ አባል ሀገራት ያሉት ብሪክስ የጋራ መገበያያ ገንዘብ እንዲፈጥሩ ይቀረበውን ሐሳብ ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ አጥብቀው ተቃውመውታል፡፡ ተንታኞቹ እንዳሉት ህንድ በራሷ ገንዘብ መናገድን በማበረታታት ላይ ነች፡፡
ትረምፕ የብሪክስ ሃገራት ዶላርን የሚተካ የራሳቸው መገበያያ ገንዘብ የሚፈጥሩ ከሆነ መቶ በመቶ ታሪፍ እንደሚጠብቃቸው ዝተዋል፡፡
ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱት የብሪክስ ቡድን በዚህ ዓመት ኢራንን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽን ጨምሮ ተስፋፍቷል፡፡
ትረምፕ ትሩዝ ሶሻል በተባለው ማኅበራዊ መገናኛቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ "እነዚህ ሀገራት አዲስ የብሪክስ ገንዘብ እንደማይፈጥሩ ወይም ኃያሉ የአሜሪካ ዶላር በሌላ መገበያያ እንዲተካ እንደማይደግፉ ቃል እንዲገቡ እንፈልጋለን" ብለዋል፡፡
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 በዩናይትድ ስቴትስ የተመራ ማዕቀብ በሩሲያ ላይ ከተጣለ እና በቻይና እና በምዕራቡ ዓለም መካከል ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥረቶች እየተባባሱ መምጣታቸውን ተከትሎ ብሪክስ “አዲስ የመገበያያ ገንዘብ ይፍጠር” የሚለው ሐሳብ በይበልጥ ተንቀሳቅሷል፡፡
ሩሲያ እና ቻይና ላለው ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ ከዶላር ሌላ በተለያዩ ገንዘቦች ሰፋ ብሎ እንዲካሄድ ለማድረግ የሚቻልበትን መንገድ ለመቃኘት ፍላጎት እንዳላቸው በይፋ ገልጸዋል፡፡ ኒው ዴልሂ ግን ከአሜሪካ ዶላር መገበያየቷን ለመተው ፍላጎት እንደሌላት የሕንድ ወጪ ንግድ ድርጅቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አጃይ ሳሃይ ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡
መድረክ / ፎረም