በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ከወጣት የአፍሪካ ሃሳብ አፍላቂዎችና መሪዎች ጋር ተገናኙ


ተሰብሳቢዎቹ በውይይት ላይ
ተሰብሳቢዎቹ በውይይት ላይ

ጉባኤው እስከ ሀሙስ ድረስ ይቀጥላል

ከ45 የአፍሪካ አገሮች የተሰባሰቡት 115 ወጣቶች ዛሬ ማለዳ በውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ለአራት ቀናት የሚዘልቀውን ውይይታቸውንና የልምድ ልውውጥ መርሃ-ግብራቸውን ጀምረዋል።

እነዚህ በሚኖሩበት አገር በአነስተኛና ከፍተኛ የማህበራዊ መሪነት ጉልህ ሚና የተጫወቱ ወጣቶች ለአፍሪካ የወደፊት ተስፋዎቿ፣ አሁን ደግሞ የእድገት ክንዶቿ ናቸው ሲሉ የዩናይትድ ስቴይትስ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆኒ ካርሰን በስብሰባው መክፈቻ ተናግረዋል።

በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ-ግዛት ነጻ የወጡበትን 50ኛ አመት በማክበር ላይ ባሉበት ወቅት የወደፊትና የአሁን የአህጉሪቷን መሪዎች አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አምነው ነው ፕሬዝደንት ኦባማ በዋይት ሃውስ እነዚህን ወጣቶች ለውይይት የጠሩት።

ወደ ዋይት ሃውስ ከማምራታቸው በፊት ግን እነዚህ ወጣቶች እርስ በርስ በተለያዩ ጉዳዮች ተወያይተዋል።

በርካታ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶችና ልምዶችን ከየአገራቸው ይዘው የመጡት ወጣቶች እርስ በርስ እየተማማሩ ችግሮቻቸውን ከባለሙያዎች ጋር እየተወያዩ አርፍደዋል።

ከኢትዮጵያም 4 ተሳታፊዎች መጥተዋል። አንዳንዶቹ በወጣቶች ማህበር የተሰባሰቡ አቀንቃኞች ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ እጅጊያቸውን ሰብስበው በስራ ላይ የተሰማሩ ናቸው።

ይሄ ስብሰባ ታዲያ ለሁሉም ነው። ግንዛቤ መፍጠር፣ አቅም መገንባትና የተሰሩ ተግባራዊ ስራዎችን ደግሞ ለሌሎች ማሳየት ነው አላማው።

እኛ የወጣት ጉዳይን ይዘው በየስብሰባው ለሚሳተፉ ቦታ የለንም፤ በስራ የተሰማራችሁ ካላችሁ ግን ስራችሁን አሳዩንና ወደ ትልቅ ደረጃ እናድርሰው ሲሉ የተናገሩት ደግሞ TED የተባለው የፈጣሪ ጭንቅላት ያላቸውን አፍሪካዊያን ወጣቶች የሚያግዝ ድርጅት ነው።

ድርጅቱ ለምሳሌ በመንደራቸው ከንፋስ መዘውር የሚሰራ የሀይል ማመንጫ እንደገነባው የማላዊው የ12 አመት ወጣት ዊሊያም ኳምክእ`ምባ አይነት ፈጣሪዎችን ያግዛል። በቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚገኙ እድገቶችን፣ ማህበራዊ ችግሮችን የመፍቻ አዲስ መንገዶችን፤ ሰርቶ የማደርና ኑሮን የማሸነፍ ውጤቶችን ያበረታታል።

በዚህ ጉባኤ የሚሳተፉት ወጣቶች ታዲያ እንዲህ ያለ ድጋፍ ከሚሰጡ ድርጅቶች ተወካዮችም ጋር ይወያያሉ፣ ሃሳብ ይለዋወጣሉ፣ ተዋውቀውም ወደፊት ለሚሰሩት ስራ ድጋፍ ያመቻቻሉ።

ይህንን ነው ፕሬዝደንት ኦባማም የአፍሪካ ወጣቶች እንዲያደርጉ አስበው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ የጠሯቸው።

XS
SM
MD
LG