“የዓለም መሪዎች፣ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ የሃገሪቱ ጦር በዓለም ያለውን ወቅታዊ አቋም ለመገምገም መነሳታቸው፣ አሜሪካ ጥሎ ለመውጣት አስባ መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል” ሲሉ አዲሱ የአሜሪካ መከላከያ ምኒስትር አስታውቀዋል።
ፒት ሄግሴት ይህን ያስታወቁት በአውሮፓ የአሜሪካ ዕዝ እና በአፍሪካ የአሜሪካ ዕዝ ዋና መሥሪያ ቤቶች በሚገኙበት ስቱትጋርት ጀርመን ከጋዜጠኞች ጋራ በነበራቸው ቆይታ ነው። ፒት ሄግሴት ሥልጣን ከያዙ በኋላ የውጪ ጉዞ ሲያደርጉ የመጀመሪያው ነው።
“በሁሉም ሥፍራ የአሜሪካ ጦር ያለበትን ሁኔታ ካልገመገምን ቸልተኝት ነው የሚሆነው፣ አሜሪካ ትታ ልትሄድ ነው የሚለው ግምት ግን ስህተት ነው” ሲሉ ተደምጠዋል የመከላከያ ምኒስትሩ።
የመከላከያ ምኒስትሩ ጀርመን የተገኙት የኔቶ መከላከያ ምኒስትሮች እና ‘የዩክሬን የመከላከያ ኮንትራት ቡድን’ የተሰኘው አካል የሚያካሂዳቸው ስብሰባዎችን ለመካፈል ነው። ቡድኑ 50 ሃገራትን ያቀፈና ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ለመቀልበስ የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቃል የገባ እንደሆነም ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም