በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩክሬኗ ካርኪቭ በአየር ተደበደበች


 በካርኪቭ በአየር ድብደባው የተጎዳውን ሕንፃ
በካርኪቭ በአየር ድብደባው የተጎዳውን ሕንፃ

ከተጀመረ ስድስተኛ ቀኑን በያዘው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የዩክሬኗ ሁለተኛ ግዙፏ ካርኪቭ ከተማ በሩሲያ ኃይሎች ከፍተኛ የሆነ የአየር ድብደባ የተፈጸመባት ሲሆን የሩሲያ ኃይሎችም ወደ ዋና ከተማዋ ኪየቭ እያመሩ ይገኛሉ፡፡

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥርያ ቤት መሃል ካርኪቭ ከተማ የሚገኘው የክልሉ የመንግስት ቢሮ ሕንጻ አካባቢ መኪኖች እየተመላለሱ ባለበት ሰዓት በተፈጸመ የአየር ጥቃት ከፍተኛ የሆነ የእሳት አረር እና ጭስ የሚያሳይ ቪዲዮ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ “ሩሲያ ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ሕጎችን በጣሰ መልኩ ጦርነት እያካሄደች ነው” በማለት በትዊተር ገጹ ላይ ጨምሮ ያስታወቀ ሲሆን አያይዞም “የሩሲያ ዋና ትኩረት ትላልቅ ከተሞችን በሚሳይል ማጥቃት፣ እንዲሁም ሲቪሎቭን መግደል እና የሲቪሎች መገልገያ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማውደም ነው” ሲል አስፍሯል፡፡

በሥፍራ ሰለደረሱ ጉዳቶች የተሰሙ ነገሮች ባይኖሩም የካርኪቭ ባለሥልጣናት በጥቃቱ የተነሳ ከ10 በላይ የሚሆኑ ሰዎች መቁሰላቸውን እና ሌሎች 11 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቀዋል፡፡

ከኪየቭ በስተሰሜናዊ አቅጣጫ ያሉት የሩሲያ ሃይሎች በዋና መዲናዋ ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ ከፍተኛ የሆነ ፍርሃት አሳድሯል፡፡ ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ባለሥልጣናት እና የብሪታኒያ የደህንነት ቢሮ ከዋና ከተማዋ በ25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የሚገኙት የሩሲያ ወታደሮች በቅርብ ቀናት ምንም ያህል አለመጓዛቸውን ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል፡፡ ማክሳር በተሰኘው የሳተላይት ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሰኞ ዕለት የተነሳ ምስል 64 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው የሩሲያ ሰራዊት ምስልን ማንሳት ችሏል፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዘዳንት ቮልዴሚየር ዘለንስኪ ሰኞ ዕለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት “ጠላታችን ዒላማው ኪየቭ ስትሆን ወደ ዋና ከተማዋ አናስገባቸውም ሊያጠፉን የመጡትን ትጥቅ እናስፈታቸዋለን” ብለዋል፡፡

ሰኞ ዕለት ሁለቱ ሃገራት 5 ሠዓታትን የፈጀ ውይይት ቢያደርጉም ዩክሬን የሩሲያ ወታደሮች ጦርነቱን ሙሉ ለሙሉ አቁመው ከግዛቷ እንዲወጡላት የጠየቀች ሲሆን፤ ሁለቱ ሃገራት ለጉዳያቸው ዕልባት ሳያበጁ ተለያይተዋል፡፡ ምንም እንኳን ሌላ ቀነ ቀጠሮ ባይዙም ሃገራቱ በድጋሚ እንደሚገናኙም ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ በጦርነቱ ምክንያት በተፈጠረ የሰብዓዊ ቀውስ እስካሁን ድረስ 520,000 የሚደርሱ ስደተኞች ወደ ጎረቤት ሃገራት መፍሰሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

XS
SM
MD
LG