ሄሬኬን ‘በሪል’ የሚል መጠሪያ በተሰጠው እና በደቡብ ማዕከላዊ ዩናይትድ ስቴትሷ የቴክሳስ ክፍለ ግዛት የደረሰው ከፍተኛ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናም የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ ባስከተለባቸው አካባቢዎች ለሕልፈት የተዳረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ተገለጠ። ዝናም አዘሉን አደገኛ አውሎ ነፋስ ተከትሎ 23 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
የሃገሪቱ አራተኛ ትልቅ ከተማ ሂዩስተን የተቋረጠውን መጠነ ሰፊ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመቀጠል ከአንድ ሳምንት በላይ መፍጀቱም ተዘግቧል። ሄሬኬን ‘በሪል’ ቁጥሩ 3 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያገኝ የነበረውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲቋረጥ ማድረጉን ተከትሎ፣ ከከፍተኛ ሙቀት ጋር ለተዛመዱ የሕመም ዓይነቶች ተጋልጠው የሕክምና እርዳታ ፍለጋ የሚመጡት ሰዎች ቁጥርም በከፍተኛ ደረጃ ማሻቀቡን የሕክምና ተቋማት አመልክተዋል።
ባለሞያዎች አክለው እንዳመለከቱት፣ በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር በውል ተለይቶ ከመታወቁ በፊት ሳምንታት እና ዓመታት ሊወስድ ይችላል። ሆኖም ትክክለኛውን መንስኤዎች ማወቁ ለወደፊት እቅድ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
መድረክ / ፎረም