በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋዛ የስደተኞች መጠለያ በደረሰ የአየር ጥቃት 70 ሰዎች መገደላቸውን የጤና ባለስልጣናት ገለፁ


የቦምብ ጥቃቱን ተከትሎ በአካባቢው ጭስ ይታያል
የቦምብ ጥቃቱን ተከትሎ በአካባቢው ጭስ ይታያል

ትናንት ዕሁድ ማምሻውን እስራኤል ማዕከላዊ ጋዛ ውስጥ በሚገኝ የስደተኞች ካምፕ ላይ ባካሄደችው የአየር ጥቃት 70 ሰዎች መገደላቸውን ሐማስ የሚያስተዳድረው የጋዛ ሰርጥ የጤና ባለስልጣናት አስታወቁ።

እስራኤል በበኩሏ ማጋዚ በተሰኘው ስፍራ ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት ምርመራ እያካሄደች መሆኗን ገልፃ፣ የሐማስን ታጣቂ ቡድን ለማጥፋት በምታደርገው ጥረት ሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቁርጠኝነት እንዳላት በድጋሚ ገልጻለች።

በተጨማሪም እስራኤል ከአርብ ወዲህ 17 ወታደሮቿ በጦርነቱ መሞታቸውን በመግለፅ፣ የምድር ላይ ዘመቻ ከከፈተች ወዲህ የሞቱባት ወታደሮች ቁጥር 156 መድረሱን አስታውቃለች።

ከምድር ጦር ሌላ በሺዎች የሚቆጠሩ የአየር ላይ ጥቃቶችን ያካተተው የእስራኤል ዘመቻ፣ አብዛኛውን የጋዛ ክፍል ያፈራረሰ ሲሆን ከ20ሺህ 400 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ ጤና ሚኒስትር አስታውቋል። በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ 2.3 ሚሊየን ሰዎችም እጅግ በተጨናነቁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።

እ.አ.አ ከታህሳስ 20 ወዲህ፣ ጋዛ የሚገኙ ሆስፒታሎችን እና አምቡላንሶችን ጨምሮ፣ 246 የጤና ተቋማት ላይ ጥቃት መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት የመዘገበ ሲሆን፣ 582 ሰዎች መሞታቸውን እና 748 መቁሰላቸውን ጨምሮ ገልጿል።

ሐማስ የተጨናነቁ መኖሪያ ቤቶችን እና የምድር ውስጥ መተላለፊያዎችን ለመደበቂያነት መጠቀሙ፣ “ከፍተኛ ቁጥር ላለው የዜጎች ሞት ተጠያቂ ነው” በማለት እስራኤል ትከሳለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG