በአሜሪካ በምግብና ሸቀጦች ላይ አላግባብ የሚደረግን የዋጋ ጭማሪ በፌዴራል ደረጃ እገዳ እንደሚጥሉበት እንዲሁም ለአዲስ ቤት ገዢዎች 25ሺሕ ዶላር እንዲሰጥ እንደሚያደርጉ ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት ካመላ ሄሪስ ዛሬ ዓርብ የኢኮኖሚ ዕቅዳቸውን ይፋ በሚያደርጉበት ንግግር ያሳውቃሉ ተብሏል።
በኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ የመጀመሪየ በሚሆነው ንግግራቸው፣ እየናረ የመጣውን የምግብ ሸቀጦችና የቤት ዋጋን በተመለከተ ያላቸውን መፍትሄ ይፋ ያደርጋሉ።
ካመላ ሄሪስ ንግግራቸውን የሚያደርጉት እርሳቸውም ሆነ የሪፐብሊካኑ እጩ ዶናልድ ትረምፕ ለማሸነፍ ከፍተኛ ፍልሚያ ከሚያደርጉበት ግዛቶች አንዷ በሆነችው ሰሜን ካሮላይና ነው።
ካመላ ሄሪስ በምርጫው አሸንፈው ዋይት ሃውስን ከተቆጣጠሩ፣ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት በአሜሪካ የናረውን የግሮሰሪ እና የቤት ዋጋ ለማርገብ እንደሚሠሩ የምርጫ ዘመቻ ቡድናቸው ለዜና ሰዎች በላከው ማስታወሻ ላይ አመልክቷል።
ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ትርፍ ለማጋበስ ሲሉ ሸማቾችን መጉዳት እንደሌለባቸው፣ በተለይም የሥጋ አቅራቢ ዘርፉ ለገበሬዎች አነስተኛ ዋጋ በመስጠት ለሰማቾች ግን በከፍተኛ ዋጋ የሚያቀርብ በመሆኑ፣ ካመላ ሄሪስ ይህን ማስቆም እንደሚሹ የዘመቻ ቡድናቸው ጨምሮ አስታውቋል።
የሄሪስን ሃሳብ የሰሙት ዶናልድ ትረምፕ፣ “የኮሚኒስት የዋጋ ቁጥጥር” ሲሉ ገልጸውታል።
“ሃሳቡ አለመስራቱ ብቻ ሳይሆን፣ ተቃራኒውን ውጤት ያመጣል፣ የምግብ እጥረትን እና ረሃብን ብሎም የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል” ሲሉ አክለዋል ትረምፕ፡፡
በአሜሪካ ኢኮኖሚ፤ የገንዘብ ፖሊስውን፣ የወለድ መጠንና ሌሎችንም ጉዳዮች በገለልተኝነት የሚወስነው አካል ፌዴራል ረዘርቭ በመሆኑ፣ ፕሬዝደንታዊ ፖሊሲዎች ዋጋን በመቀነስ ረገድ ቢያንስ በአጭር ግዜ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ተጽእኖ እንደማይኖራቸው የኢኮኖሚ ተንታኞች ይገልጻሉ።
መድረክ / ፎረም