በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሃሪስ የአክራ ንግግር የአሜሪካ እና አፍሪካ አጋርነትን ዐዲስ ምዕራፍ ያጎላል


የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የጋና ጉብኝታቸውን ቀጥለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የጋና ጉብኝታቸውን ቀጥለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ የጋና ጉብኝታቸውን ቀጥለዋል። ለአንድ ሳምንት የሚቆየውን፣ የሦስት የአፍሪካ አገሮች ጉብኝታቸውን ትላንት ጋና ላይ የጀመሩት ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ፣ በዛሬው ዕለት በዋና ከተማዋ አክራ “ብላክ ስታር ጌት” አደባባይ በሚያደርጉት ንግግር፣ የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ አጋርነት ወደ ዐዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መኾኑን አጉልቶ የሚያሳይ እንደሚኾን ተመልክቷል።

ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ፣ በባርነት የተያዙ አፍሪካውያን፣ በመርከብ ተጭነው ወደ አሜሪካ ይጋዙበት የነበረውን የባሪያ ፍንገላ መናኸሪያ፥ “ኬፕ ኮስት ካስል” ጎብኝተዋል።

የዩናይትድ ስቴትሷ ምክትል ፕሬዚዳንት ትላንት ሰኞ ከጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ ጋራ ኾነው፣ በአክራ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት በአደረጉት ንግግር፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋራ ባላት ግንኙነት፣ ጥቅሟ ከቻይና ጋራ ካላት ፉክክር በላይ እንደኾነ አስገንዝበዋል።

"ለሁከት፣ ጽንፈኝነት እና አለመረጋጋት መፍትሔ ለመፈለግ ይረዳ ዘንድ፣ ለቤኒን፥ ለጋና፥ ለጊኒ፥ ለኮት ዲቯር እና ለቶጎ፣ የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ መመደባችንን ስገልጽ በደስታ ነው። ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የዩናይትድ ስቴትስ፥ ግጭቶችን መከላከልንና ጸጥታን ማጠናከርን በሚመለከተው ስትራቴጂዋ ውስጥ፣ በምዕራብ አፍሪካ ጠረፍ ላይ የሚያተኩረውን ዕቅድዋን፣ ባለፈው ሳምንት አስተዋውቀዋል። አሁን ይፋ ያደረግኹት ድጋፍ፣ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል። ቀጣናውን፣ ጸጥታን፣ አስተዳደርንና ልማትን ለሚመለከቱ ጉዳዮች ድጋፍም ይውላል፤” ሲሉ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ አብራርተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ፣ እስላማዊ ጽንፈኝነት እየተስፋፋ ለሚገኝበት የሣህል አካባቢ፣ በአብዛኛው ግጭቶችን ለመከላከል ለሚደረጉ ጥረቶች ድጋፍ የሚውል 139 ሚሊዮን ዶላር መመደቧን፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ፣ ትላንት ጋና ላይ ይፋ አድርገዋል።

ካማላ ሃሪስ፣ በዚህ ዓመት አፍሪካን በመጎብኘት፣ አምስተኛዋ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን ናቸው።

ቻይና፣ በአፍሪካ አገሮች ግዙፍ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እያካሔደችና የብዙ ቢሊዮን ዶላር ብድር እየሰጠች ሲኾን፤ ብዙ ታዛቢዎች፣ እንቅስቃሴዋን ለማስፋፋት እና ተጽእኖዋን ለማጠናከር የያዘችው ትግል አድርገው ይመለከቱታል።

አገራቸው፣ የአፍሪካ አገሮችን የምትመለከታቸው፣ ከቻይና ጋራ ከያዘችው ፉክክር አኳያ ነው፤ የሚሉ ትችቶችን፣ ምክትል ፕሬዚዳንቷ ውድቅ አድርገዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንት ሃሪስ፣ ጉብኝታቸውን ቀጥለው፣ በነገው ዕለት ወደ ታንዛንያ ከዚያም ወደ ዛምቢያ ይጓዛሉ።

XS
SM
MD
LG