ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ሙኒክ ላይ በሩሲያ እና በዩክሬን ቀውስ ጉዳይ ከአጋሮቻቸው ጋር ይመክራሉ።
የዩናይትድ ስቴትስን የልዑካን ቡድን የመሩት ሃሪስ በሙኒክ የፀጥታ ጉባኤ ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ፣ የኔቶ ዋና ፀኃፊ የንስ ስቶልተንበርግ፣ የላትቪያ፣ የሊትዌኒያ እና የኢስቶኒያ መሪዎች ጋርም ተገናኝተው ይነጋገራሉ።
ሃሪስ ከነገ በስቲያ ቅዳሜ የባይደን አስተዳደር ባለሥልጣናት በዲፕሎማሲያዊ፣ ወታደራዊ እና የምጣኔ ሃብት መስክ በምዕራባውያን አገሮች እና የኔቶ አባላት መካከል “ታየ” ባሉት የአንድነት ጥንካሬ መንፈስ ላይ ትኩረት ያደረገ አብይ ንግግርም ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አንድ ከፍተኛ የአስተዳደሩ ባለስልጣን ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ስተያየት ምክትል ፕሬዚዳንቷ በንግግራቸው “አንድነት ሩሲያ ለምትከተለው ማንኛውም ዓይነት የጠብ አጫሪነት አዝማሚያ በማያወላውል ፍጥነት ምላሽ ለመስጠት የሚያስቻለን የጥንካሬያችን ምንጭ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ይናገራሉ።" ብለዋል።
“ሃሪስ በንግግራቸው በተጨማሪም የሩስያን ወረራ ለመቋቋም እና ኔቶን ለማጠናከር ያለንን ቁርጠኝነት ያረጋግጣሉ። ‘ዩክሬይንን የመውረር ፍላጎቷ ሩስያን ይበልጥ ደካማ እንጂ ጠንካራ አገር አያደርጋትም’ ብለው እንደሚያምኑም የሚያመላክቱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ባለሥልጣናቱ አክለውም የጉዟቸው አብይ ዓላማ የምዕራባውያን አጋሮች የተቀናጀ እና ቀጣዩን አቅጣጫ አስመልክቶም ለሩሲያ ግልጽ መልእክት ለማስተላልፍ መሆኑን አመልክተዋል።
"የእኛ ምርጫ ዲፕሎማሲ እና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስድ አማራጭን የሚያከላክሉ እርምጃዎች ናቸው። ነገር ግን ሩሲያ ጠብ አጫሪነትን ከመረጠች ዝግጁ ነን" ሲሉ የአስተዳደር ባለሥልጣን ተናግረዋል።