በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የግለሰብ ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ተሰብረው ባልታወቁ ሰዎች መወሰዳቸውን ባለቤቶቻቸው ተናገሩ


በሐረር ከተማ “ገልመሺራ” በተባለ የመኖሪያ ሰፈር
በሐረር ከተማ “ገልመሺራ” በተባለ የመኖሪያ ሰፈር

በሐረሪ ክልል የሚገኙ የኮንዶሚኒዬም ቤት ባለቤቶች፤ ቤቶቻቸው እየተሰበሩ ባልታወቁ ሰዎች መወሰዳቸውን ተናገሩ። ቅድሚያ ገንዘብ ከፍለው ቁልፋቸውን የተረከቧቸውንና የውስጥ ግንባታ እያከናወኑ ያሉባቸው ቤቶች እየተሰበሩ የማያውቋቸው ሰዎች መኖሪያ መሆኑን በመግለፅ አቤቱታ እያሰሙ ነው። የክልሉ ቤቶች ልማት ቢሮ በበኩሉ ለደንበኞቹ ያስተላለፋቸው ቤቶችና ለመምሕራን እየተገነቡ ያሉም ቤቶች ተወስደዋል ብሏል።

የግለሰብ ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ተሰብረው ባልታወቁ ሰዎች መወሰዳቸውን ባለቤቶቻቸው ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:59 0:00

በሐረር ከተማ “ገልመሺራ” በተባለ የመኖሪያ ሰፈር ከተገነቡ 600 ኮንዶሚኒዬም ቤቶች ውስጥ ባለቤቶቻቸው መኖር ያልጀመሩባቸውና በውስጥ ግንባታ ላይ የሚገኙ 30 የሚደርሱ የኮንዶሚኒዬም ቤቶች በር ተሰብሮ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች መኖር እንደጀመሩባቸው የቤቶቹ ባለቤቶች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ቤቶቻቸው የተወሰዱባቸው ሰዎች በአንድ ላይ ሆነው አቤቱታ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። ከእነዚህ ውስጥም የቤት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዳቸውን ካሳዩን በኋላ ስማቸውን ብንጠቅስ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ግለሰብ፤ ተጣጥረው ባገኙት ገንዘብ የገዙት ቤት በማያውቋቸው ሰዎች መወሰዳቸውን ይናገራሉ።

ገልመሺራ ላይ ቤት እያደስን ነው ያለነው፡፡ ማለትም ጂፕሰም ፊኒሺንግ ሥራዎችን እየሠራን ባለንበት ወቅት ያው ማታ ዘግተን ነው የምንሄደው፤ ቀን ነው መጥተን የምንሠራው፡፡ በዚህ ሁኔታ በሩን ሰብረው ውስጡ ገብተው እየኖሩበት ነው ያሉት

ብለዋል።

ባለቤቶቹ እንደሚናገሩት፤ ቤቶቹን መውሰድ የተጀመረው ታኅሣሥ 5 ምሽት ነው። ማንነታቸው ያልታወቁ ወጣቶች የሁሉንም ኮንዶሚኒዬም ቤቶች በር በማንኳኳት ነዋሪ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ከለዩ በኋላ በማግሥቱ ነዋሪ የሌለባቸውን ቤቶች በር እየሰበሩ ያልታወቁ ነዋሪዎች ገብተው መኖር መጀመራቸውን ቅሬታ አቅራቢዎቹ ይገልፃሉ፡፡ ቤቶቻቸውን እንዲለቁላቸው ሲጠይቁም “ቤቶቹ ነፃ ናቸው ተብለን ከፍለንባቸው ነው የተረከብናቸው” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው ይገልፃሉ። ገንዘብ ተቀብለው ለአዲስ ገቢዎቹ ቤቶቹን አስረክበዋል የተባሉት ሰዎች ማንነት ግን ማወቅ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

የኮንዶሚኒዬም ቤቶችን ገንብቶ ለነዋሪዎች የሚያስተላልፈው የቤቶች ልማትና የመንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢሊ አብዱራሂም በበኩላቸው ከኮንዶሚኒም ባለቤቶች ባሻገር ኤጀንሲያቸው እየገነቧቸው የነበሩ ለመምሕራን ሊተላለፉ የታሰቡ 60 ኮንዶሚኒዬም ቤቶችም ተሰብረው ማንነታቸው ያልታወቁ ነዋሪዎች እየኖሩባቸው ነው ብለዋል።

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፀጥታ መታወክ ጋር በተያያዘ እዚያ አካባቢ በተለይ ምሽት ላይ ቤት እየሰበሩ ማንነታቸው የማይታወቁና ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ግለሰቦች ቤት እየሰበሩ እንደሚገቡባቸው እኛ ጋር በመምጣት እያመለከቱ ይገኛሉ። እስካሁን ድረስም ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች እየመጡ ቅሬታቸውን እያቀረቡ ነው።” ብለዋል።

አቶ ኢሊ አብዱራሂም አያይዘውም፤ “በእኛም በኩል ደግሞ ቅድም እንደነገርኩህ 100 ቤት ካልናቸው ውስጥ 40ዎቹን አስተላልፈን 60ዎቹ ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ኮንትራክተሩ ያላስረከበበት ሁኔታ ነበረ። እነሱንም ሰብረው ገብተውባቸዋል። ቤቶችም

"ከሁለት ወር በፊት ለመምሕራን በእጣ የተላለፉበትና መምሕራን የነበረባቸውን የቤት ችግር ይፈታላቸዋል ብለን አስበን ያዘጋጀነው ነበር እነሱም 60 ቤቶች ተሰብረው ተወስደዋል"

።” ብለዋል።

የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ለባለዕድሎቹ የሚተላለፉት በር መግጠምና ጂፕሰም ወይም ቀለም መቀባትን የመሳሰሉ የማጠናቀቂያ ሥራቸው ሳይሠራ ነው። ውስን አቅም ያላቸው አንዳንድ ባለ ዕድሎችም ቤቱን ለገዙበት በየወሩ ለባንክ ከሚከፍሉት ክፍያ ባሻገር የቤቱ የማጠናቀቂያ ሥራ የሚፈልገውን ገንዘብ በአንዴ ማሟላት አይችሉም። በዚህ ምክንያት የተረከቧቸውን ቤቶች ቶሎ አጠናቅቀው መኖር እንዳልጀመሩ ይናገራሉ። የቤቶቹ ዋጋ ከ191 ሺ እስከ 260 ሺ ድረስ ነው። ባለ ዕድሎቹም በመነሻነት ከ28ሺ እስከ 42 ሺ ብር ከከፈሉ በኋላ በየወሩ ከደሞዛቸው ወይም ወርሃዊ ገቢያቸው ላይ ገንዘብ እየተቆረጠ ለባንክ ገቢ ያደርጋሉ፤ በአሁኑ ሰአትም አብዛኞቹ ዕድለኞች ከ100ሺ ብር በላይ የኮንዶሚኒዬም እዳ መክፈላቸውን ይናገራሉ።

በየወሩ ይህንን እየከፈሉ በአማካይ ከ50ሺ ብር ያላነሰ ወጪ የሚጠይቀውን የቤት በርና መስኮት የመግጠምና ሌሎችን የማጠናቀቂያ ሥራዎች በተደራቢነት ለመሥራት አቅም የሌላቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ቤቶቻቸው ተሰብረው የተወሰዱባቸው አብዛኞቹ ባለዕድሎችም እነዚህ ናቸው፤ የቤቶቻቸውን ግንባታ አጠናቀው ለሦስተኛ ወገን ያከራዩ የነበሩና ተከራይ የለቀቃቸው ቤቶችም መወሰዳቸን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

አቶ ኢሊ አብዱራሂም በበኩላቸው ቤቶቹን የውስጥ ይዞታ ሳያጠናቅቁ ለባለቤቶቹ እንደሚያስረክቡ ገልፀው ተሰብረው የተወሰዱት በዚህ መልክ የተሰሩ ቤቶች እንደሆኑ ይናገራል። “ የኛ ግንባታ ስታንዳርድ አለው። ሙሉ በሙሉ ቀለም ቀብተን አይደለም የምናስተላልፈው። ለኑሮ አመቺ አድርገን ቀሪውን ባለቤቱ ራሱ ገንብቶ የሚስተላልፍበት ሂደት አለ። ይሄ ከረዢም ጊዜ ጀምሮ እየተሠራበት ያለና ሐረር ላይ ያሉ በዚህ መልኩ ነው የተላለፉት። ሌላ ቦታም በዚህ መሰረት ነው የሚሰራው። የቤቱ ባለቤት ራሱ አቅሙ በሚፈቅደው መሰረት ቤቶቹን እንዲያጠናቅቅ ተደርጎ ይተዋል። በአቅም ምክንያት ቤታቸውን ቶሎ አጠናቀው ያልገቡበት አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በግል ችግር ምክንያት፣ በሕግ የተያዙ ኬዞች፣ ከትዳር ጋር የተያያዘ ሊሆ ይችላል፣ የሞቱ ግለሰቦችም እንዳሉ መረጃዎች አለን።” ብለዋል። ማንነታቸው ያልታወቁ ያሏቸው ግለሰቦችም በዚህ መልክ ነው ቤቶቹን ሰብረው ገብተው መኖር የጀመሩት ብለዋል።

የኮንዶሚኒዬም ባለቤቶችና የቤቶች ልማትና የመንግሥት ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ድርጊቱን ለፖሊስ አሳውቀው ምላሹን እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የክልሉ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምላሻቸውን እንዲሰጡን ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

የሐረሪ ክልል በሐረሪ ብሔራዊ ሊግ (ሐብሊ) እና በኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጥምረት የሚተዳደር ሲሆን ክልሉ በርካታ ቅሬታዎች የሚቀርቡበት ነው፡፡ ሐብሊ ከወር በፊት የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር የቀየረ ሲሆን ኦዴፓ ደግሞ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የፍትህና ፀጥታቢሮ ኃላፊን ጨምሮ ቁልፍ አመራሮቹን ከሁለት ሳምንት በፊት ቀይሯል፡፡ አሁን የክልሉ ነዋሪዎች እነኚህ የተቀየሩ አዳዲስ አመራሮች ለውጥ ያመጡ ከሆነ እየተጠባበቁ መሆናቸውን ይናገራሉ። አዲሱ የፍትህና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ዩሱፍም አስተዳደራቸው ባጠቃላይ የክልሉ ነዋሪዎችን ቅሬታዎች እያጠና እንደሆነና በቅርቡ ተጨባጭ ሥራዎችን ሠርተው ለውጥ እንደሚያመጡ አሁን ግን ከአዲስነታቸው አንጻር ዝርዝር አስያዬት መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ የቢሮ ኃላፊውም ሆኑ የፖሊስ ኮሚሽኑ አመራሮች በጉዳዩ ዙሪያ የሚሰጡንን አስተያየት ይዘን እንመለሳለ።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG