በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"እጃችሁን ከአፍሪካ ላይ አንሱ" - አቡነ ፍራንሲስ


የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

የሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፍራንሲስ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ለሚገኙ ቁጥራቸው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለተገመቱ አማኞች ዛሬ ረቡዕ ባሰሙት ንግግር ሰዎች ከማዕድን በላይ የበለጸጉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለኮንጎ ዜጎችም የሰላምና የይቅርታ መልዕክታቸውንአስተላልፈዋል፡፡

በኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን የ6 ቀናት ጉብኝታቸውን ትናንት ማክሰኞ የጀመሩት አቡነ ፍራንሲስ በአፍሪካ የግጭት መንስኤ ነው ያሉትና “የስስት መርዝ” ብለው የጠሩት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

በተለይም የበለጸገው ዓለም፣ “ከምድር በታች ካሉት ማዕድኖች በላይ ሰዎች የተከበሩ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል” ሲሉም ሊቀ ጳጳሱ አሳስበዋል፡፡

“እጃችሁን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላይ አንሱ! እጃችሁን ከአፍሪካ ላይ አንሱ! አፍሪካን ማነቃችሁን አቁሙ አፍሪካ ማዕድን የሚዘረፍባት የምትበዘበዝ መሬት አይደለችም፡፡” ያሉት ፍራንሲስ “የአፍሪካ መሬቶች በአጠቃላይም ጠቅላላው የአፍሪካ አህጉር አሁን ድረስ የተለያዩ መልኮች ላሏቸው ብዘበዛዎች መጋለጣቸው አሳዛኝ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ ምእመናኑ እና የኮንጎ ዜጎችም፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ለአስርት ዓመታት ሲያውኩ ለነበሩት ሁሉ ይቅርታ እንዲያደርጉ እና “የምህረት ልብ” እንዲኖራቸው አሳስበዋል፡፡

“ልባችንን ከቂምና ጠላትነት፣ ከቁጣና ከቂም በቀል ማጽዳት ምንኛ መልካም ነገር ነው” ብለዋል ፍራንሲስ፡፡

የ86 ዓመቱ አቡነ ፍራንሲስ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጉብኝት እኤአ በ1985 አቡነ ጆን ፖል ሁለተኛ ካደረጉት ጉብኘት ቀጥሎ የመጀመሪያው መሆኑ ተነግሯል፡፡

ለሊቀጳጳሱ ተለይታ በተዘጋጀቸው ልዩ ተሽከርካሪ ከኪናሻሳው የናዶሎ አውሮፕላን ማረፊያ የወጡትን የሮማ ካቶሊክ ቤተርስቲያን መሪ፣ በሺዎች የሚቆጥሩ አፍቃሪዎቻቸው የተቀበሏቸው ሲሆን ብዙዎቹም ሴቶች በአቡነ ፍራንሲስ ምስል ያጌጡ ልቦሶችን ለብሰው ታይተዋል፡፡

95 ሚሊዮን ከሚገመተው የኮንግ ህዝብ ቢያንስ ግማሽ ያህሉ የካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆኑም ተገልጿል፡፡

XS
SM
MD
LG