ሰዓሊ፣ የሥነ ስዕል አስተማሪ እና የዓለም ጋለሪ (የሥነ ጥበብ ማዕከል) መስራች ነች፣ አርቲስት ዓለም ጌታቸው፡፡
ከ12 ዓመቷ ጀምሮ፣ እግሮቿ መራመድ እንደተሳናቸው የምትገልጸው አርቲስት ዓለም፣ ከአካል ጉዳተኝነት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ብዙ ፈተናዎች እና ውጣ ውረዶች በቀደመው በሥራ ሕይወቷም የገጠሟትን ፈታኝ እና ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያት በጽናት አልፋ፣ ዛሬ ለብዙዎች አርዓያ መሆን የምትችል ስኬታማ ሴት ሆናለች፡፡
አካል ጉዳተኝነት ህልምን ከማሳካት እንደማያግድ ብርሃናቸውን በሰፊው አብርተው ለትውልዱ በተምሳሌትነት ከተገለጡ የይቻላል አርማዎች መካከል አንዷ የሆነችው አርቲስት ዓለም፣ ከ13 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በከፈተችው ዓለም ጋለሪ ስዕሎቿን ከመሸጥ አልፋ ሌሎች ተምሳሌታዊ አገልግሎቶችንም ትሰጣለች፡፡
ዙሪያውን በማራኪ ስዕላት ያጌጠው፣ በበርካታ መጽሓፍትም የታጨቀው ዓለም ጋለሪ፣ በከተማዋ ከሚገኙ በርካታ የስዕል ጥበብ ማዕከላት የተለየ ነው፡፡ ጋለሪው በርካቶች እውቀትን የሚገበዩበት፣ በተለያዩ ማኅበረሰባዊ ጉዳዮችም ላይ የሚመክሩበት ስፍራ ነው፡፡
የስዕል ሥራዎቿን ከሀገር ውስጥ አልፋ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ለተለያዩ ሀገራትም የምታቀርበው ዓለም፣ በሥራዎቿ የተለያዩ ሽልማቶችን እና እውቅናዎችን አግኝታለች፡፡
ከስዕል ሥራዋ ጎን ለጎን የስነ ስዕል ትምህርት ቤት ከፍታ በርካታ ሰዓሊያንን ለማፍራት እንዲሁም በሐሳብ የሚሞግቱና ለሀገራቸው አንዳች ነገር ማበርከት የሚችሉ ዜጎችን ለመፍጠር የምትታትረው አርቲስት ዓለም፣ የበጎ አድራጎት ድርጅትም አቋቁማለች፡፡ ለሕጻናት የሚሆኑ መጽሓፍትን መጻፍን ጨምሮ፣ የብዙዎች ተምሳሌት የሆነችው አርቲስት ዓለም ሌሎች በርካታ ተግባራትንም ታከናውናለች፡፡