በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሄሜቲ አዲሳባ ናቸው


የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ

በሱዳን ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ስለሚቻልበት ሁኔታ ዛሬ [ሐሙስ] አዲስ አበባ ከገቡት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጄነራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎና ቡድናቸው ጋር መምከራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኤክስ ገፃቸው ላይ አስታውቀዋል።

በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎቹ መካከል ጦርነት ከጀመረ ወዲህ ጀኔራል ዳጋሎ ከሱዳን ውጭ አደባባይ ላይ ሲታዩ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።

በጦርነቱ ወቅት አድራሻቸው ሳይታወቅ የቆዩት ጄነራል ዳጋሎ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት ትናንት ረቡዕ ከዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ ጋር መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት መሆኑንም ዘገባው አመልክቷል.

ዛሬ ረፋዱ ላይ አዲስ አበባ የገቡትን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት አዛዥ ጄኔራል ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎን ቦሌ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ማረፊያ የተቀበሏቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ናቸው።

“ሄሜቲ”ም እየተባሉ የሚጠሩት ሞሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ አዲስ አበባ መግባታቸውን ያስታወቀው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንግዳው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አየር መንገድ ሮያል ጄት ንብረት ከሆነው አይሮፕላን ሲወርዱ የሚያሳዩ ምስሎችን ፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።

የበረራ መረጃዎችን የጠቀሰው ሮይተርስ ሄሜቲ ከአቡዳቢ ወደ ዩጋንዳ የበረሩት ትናንት ረቡዕ ጠዋት መሆኑን አመልክቶ ቀደም ሲል በነበረው በረራ በተመሳሳይ አይሮፕላን ስለመሳፈራቸው አለማወቁንም ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል።

አፍሪካ ቀንድ ላይ የስትራቴጂያዊ ጥቅም ትኩረት ያላትና የቀይ ባህሩን ወደብ ፖርት ሱዳንን ጨምሮ ሱዳን ውስጥ ነዋይ ለማፍሰስ ስታግባባ የቆየችው የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ከአሁኑ ግጭት በፊት ጀምሮ የሄሜቲ ጠንካራ ወዳጅና አጋር መሆኗን ሮይተርስ ጠቁሟል።

ባለፈው ወር አንድ የሱዳን ከፍተኛ ጄኔራል “የኢሚሬቶቹ መንግሥት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን ይደግፋል፤ ዩጋንዳን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች በኩል ደጋፍ እያቀበለ ነው” ብለው ነበር።

አቡ ዳቢ ሱዳን ውስጥ ውዝግቡን ለማርገብ ዲፕሎማሲያዊ ውይይትን እንደምትደግፍ ስትገልፅ ካምፓላም የተባለው “ሃሰት ነው” ብላለች።

በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎቹ መካከል የተደረገ ጦርነት ዋና ከተማዪቱን ካርቱምን ሲያወድም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰው ማፈናቀሉን፣ በዳርፉር የጎሳ እልቂትና ግድያ እንዲያገረሽ ማድረጉን ዘገባው አመልክቷል።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎቹ በቅርቡ ከሱዳን ትላልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችውን ዊድ ማዳኒን ጨምሮ ይዞታዎቻቸውን በማስፋት ፈጣን ለውጥ ማስመዝግባቸውን የዜና አውታሩ ጠቅሷል።

በሳዑዲ አረቢያና በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራውን ንግግር ጨምሮ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ግጭቱን ለማስቆም የተጀመሩ ጥረቶች ብዙም የሚታይ መሻሻል አላሳዩም።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የጋራ ልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ)ሄሜቲና የጦር ኃይሉ አዛዥ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ተገናኝተው ሊነጋገሩና ተኩስ ለማቆም ቁርጠኝነት እንዳላቸው ከሁለቱም ቃል ማገኘቱን ቢገልፅም ሁለቱም ወገኖች ግን ኢጋድ ለሚለው ስምምነትና ቃል ማረጋገጫ አልሰጡም።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG