በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሐማስ ታጋቾችን ለመልቀቅ እስራኤልም ጥቃቱን ለማቆም ተስማሙ


የሐማስ ታጣቂ ቡድን፣ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ፣ በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት የያዛቸው ታጋቾች ምስል ራማት ጋን፣ እስራኤል፣ እአአ ኅዳር 22/2023
የሐማስ ታጣቂ ቡድን፣ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ፣ በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት የያዛቸው ታጋቾች ምስል ራማት ጋን፣ እስራኤል፣ እአአ ኅዳር 22/2023

የሐማስ ታጣቂ ቡድን፣ ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ፣ በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት ከያዛቸው ታጋቾች መካከል አንዳንዶቹ፣ ከነገ ኀሙስ ጀምሮ ሊለቀቁ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡

ታጋቾቹ እንደሚለቀቁ የተጠቆመው፣ የእስራኤል ኃይሎች በጋዛ የሚያካሒዱትን የውጊያ ጥቃት ለአራት ቀናት ለማቆም የገቡትን ቃል ጨምሮ በተደረሰበት ስምምነት እንደኾነ፣ ካታር አስታውቃለች፡፡

ካታር እንዳስታወቀችው፣ ሐማስ፥ 50 ሴቶችንና ሕፃናት ታጋቾችን እንደሚፈታ ሲገልጽ፣ እስራኤል ደግሞ “ያሰረቻቸውን በርካታ ፍልስጥኤማውያን ሴቶችንና ሕፃናትን ለመፍታት” ተስማምታለች፡፡

ስምምነቱ፣ ረቡዕ ማለዳ ላይ ይፋ የኾነው፥ በካታር፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በግብጽ እየተመራ ለሳምንታት ከቆየ ድርድር በኋላ እንደኾነ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን እንደተናገሩት፣ በሐማስ የተለቀቁት ታጋቾች በርካታ አሜሪካውያንን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ስምምነቱን አስመልክቶ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሰጡት መግለጫ፣ “የካታር ሼኽ ታሚም ቢን ሃማድ አል ታኒ እና የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤል-ሲሲ፣ ከስምምነቱ እንዲደረስ ላሳዩት ወሳኝ አመራር እና አጋርነት አመሰግናለኹ፤” ብለዋል።

ባይደን አያይዘውም፣ “ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እና መንግሥታቸው፣ ይህ ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ እንዲኾንና በጋዛ የንጹሐን ፍልስጥኤማውያን ቤተሰቦችን ሥቃይ ለማቃለል፣ ተጨማሪ ሰብአዊ ርዳታ ለመስጠት የተራዘመውን የተኩስ አቁም ለመደገፍ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አደንቃለኹ፤” ብለዋል፡፡

የእስራኤል መንግሥት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ ሐማስ በሚለቃቸው 10 ተጨማሪ ታጋቾች ልክ፣ ተጨማሪ የተኩስ አቁም እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG