የሮማው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ በጋዛ ያለውን “ተስፋ አስቆራጭ” ያሉትን ሁኔታ በመቃወም ‘ሰላም እንዲሰፍን’ ጥሪ አሰምተዋል። ትላንት ማክሰኞ በአንድ የጋዛ ሆስፒታል ላይ የደረሰውንና ውድመት ያስከተለ ጥቃት ግን አላነሱም።
አቡኑ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ምዕመን ባሰሙት ንግግር “በፍልስጤም እና በእስራኤል የተጎዱትን እናስባለን” ሲሉ ይህ ጦርነት እንዳይባባስ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎችም እንዳይስፋፋ ያደረባቸውን ስጋት ገልጸዋል። ምዕመኑ ስለ ሰላም እንዲጸልይም አሳስበዋል።
"የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ በጋዛ ያለውም ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ነው።” ያሉት አቡነ ፍራንሲስ፡ “የሰብአዊ አደጋን ለመከላከል መደረግ ያለበት ሁሉ ይደረግ። ጦርነቱ ከዚህም ሊስፋፋ ይችላል። ሆኖም ጦርነት የሚፈታው ችግር የለም። ትርፉ
እልቂት፣ ጥላቻን ማስፋፋት እና በቀልንመዝራት ነው። ጦርነት መጪውን ጊዜ ያጨልማል፡” ብለዋል።
አቡኑ በትላንቱ ንግግራቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለተገደሉበት የጋዛው የአህሊ አረብ ሆስፒታል አደገኛ ፍንዳታ ያሉት የለም። የሐማስ ታጣቂ ቡድን እስራኤልን ለፍንዳታው ተጠያቂ ሲያደርግ፤ ለደረሰው አደጋ መንስኤ ያለመሆኗን የተናገረችው እስራኤል በበኩሏ፤ ‘ይልቁንም የፍልስጤሙ እስላማዊ ጅሃድ ሊያስወነጭፍ ሞክሮ ሳይሳካ የቀረው ሚሳይል ፍንዳታ ያስከተለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አለ’ ብላለች። የቡድኑ ቃል አቀባይ በእስራኤል በኩል የቀረበውን ይህን ውንጀላ አስተባብሏል።
የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ በጋዛ ያለውም ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ነው።”
ይህ በእንዲህ እንዳለ፡ ምእመናን በእስራኤል እና በሐማስ ግጭት “የአንድ ውግንና ብቻ” እንዲኖራቸው፤ ያም “የሰላም፣ የጸሎት እና የትጋት” እንዲሆን አቡነ ፍራንሲስ አሳስበዋል። በዚህም መሠረት የፊታችን ጥቅምት 16, 2016 ዓም የንስሐ ቀን ሆኖ እንዲውል እና በአገሬው የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 12 ሰዓት አንስቶ ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ እንደሚሰበሰቡ አቡኑ አስታውቀዋል። አያዘውም፡ ክርስቲያኖችም ሆኑ የሌሎች ሃይማኖቶች ተከታይ የሆኑ ሁሉ ባመቻቸው መንገድ በመሰባሰብ “ለዓለም ሰላም በአንድነት እንዲቆሙ” ጥሪ አድርገዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ ቀደም ብለው በጋዛ ያለችውን የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ በስልክ ማነጋገራቸውን የቫቲካን ሬዲዮ ዘግቧል። ቤተክርስቲያኒቱም ባሁኑ ወቅት፡ የታመሙ እና የአካል ጉዳተኞችን፣ እንዲሁም የቤተሰባቸውን አባላት እና መኖሪያቸውን ያጡትን ጨምሮ ቁጥራቸው 500 የሚደርስ ሰዎችን አስጠልላ በመርዳት ላይ መሆኗ ተገልጿል። በተያያዘ፡ ከአቡኑ ጋር መነጋገር በመቻላቸው “ትልቅ በረከት” ማግኘታቸውን የተናገሩ ሲስተር ናቢላ ሳሌህ የተባሉ አንዲት የቤተ ክርስቲያኒቱ መነኩሴ አቡኑ “በጸሎታቸው አስበውናል። ብርታትም ሰጥተውናል፡’ ማለታቸው ተዘግቧል።
መድረክ / ፎረም