የሀማስ ተደራዳሪዎች ከካይሮ ወጥተዋል። ከእስራኤል ጋራ በሚካሄደው ጦርነት አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ በካይሮ ሲካሄድ የቆየው ድርድር በመጪው ሳምንት እንደሚቀጥል የሀማስ ተደራዳሪዎቹ አመልክተዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ግብጽ እና ካታር ውጊያው ለስድስት ሳምንታት ያህል እንዲቆም ጋዛ ውስጥ በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር ያሉ ታጋቾች እና እስራኤል ከያዘቻቸው እስረኞች ውስጥም አንዳንዶቹን እንዲለቀቁ በሚጠይቀው የተኩስ አቁም እቅድ ስምምነት ላይ እንዲደረስ ጥረት ሲያደርጉ ሰንብተዋል።
ከጋዛ ሰርጥ ኃይሎቿን ሙሉ በሙሉ እንድታስወጣ ሀማስ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ያደረገችው እስራኤል አስተያየት አልሰጠችም።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥቅምት 7 ቀን ሀማስ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች እንደተገደሉባት ያስታወቀችው እስራኤል ሀማስን ለመደምሰስ ባላት እቅድ እንደጸናች መሆኗን ተናግራለች፡፡
ፍልስጣኤማውያኑ ታጣቂዎች አሁንም ወደ 100 የሚሆኑ ሰዎችን እና ሠላሳ አስከሬኖች እንደያዙ ናቸው ተብሎ ይታመናል። በሌላ በኩል የእስራኤል የጦር ኃይል ዛሬ በሰጠው መግለጫ በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ አካባቢ ጥቃት አድርሰን የታጣቂዎቹን ዋና ማዕከል ማውደሙን አስታውቋል። ኃይሎቹ ካን ዩኒስ ውስጥ ባደረሱት ጥቃት የታጣቂዎቹን የመሣሪያ ማከማቻም ማግኘታቸውን አመልክቷል፡፡
ጋዛን ከግብጽ ጋራ በሚያዋስነው “ራፋ” አካባቢ የተጠለሉ ፍልስጥኤማዊያን ተፈናቃዮች የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታያሁንን የጥቃት ማስጠንቀቂያ በመፍራት ከአካባቢው መውጣት መጀመራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልስጥኤም ሰብዐዊ ርዳታ ተጠባባቂ አስተባባሪ ጄሚ ሜክጎልድሪክ አመልክተዋል፡፡
እስራኤል ራፋህ ላይ ጥቃት ከመክፈቷ አስቀድሞ ፍልስጥኤማውያኑን ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት ቦታ እንደምታዛውር የተናገረች ቢሆንም ወዴት እንደሚላኩ ግን አላሳወቀችም፡፡
በጋዛ የሁለት ቀናት ጉብኝት አድርገው የተመለሱት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ረድኤት ባለሥልጣን የረድኤት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረስ ወይም እስራኤል ጥቃት የከፈተች እንደሆን በሚል ሁለት ዕቅዶችን እያዘጋጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
መድረክ / ፎረም