በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሐማስ የግብፅን የሰላም ሐሳብ ለማጤን ወደ ካይሮ ያቀናል


ፍልስጤማውያን ጥቃት ከደረሰ በኋላ ከደጃቻቸው የደረሰውን ውድመት እየተመለከቱ ራፋ ደቡብ ጋዛ እአአ ታህሣስ 29/2023
ፍልስጤማውያን ጥቃት ከደረሰ በኋላ ከደጃቻቸው የደረሰውን ውድመት እየተመለከቱ ራፋ ደቡብ ጋዛ እአአ ታህሣስ 29/2023

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም ግብፅ ያቀረበችውን የሰላም ሀሳብ ለማጤን፣ የሐማስ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዛሬ አርብ ካይሮ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ግብፅ ያቀረበችው በሶስት ደረጃ የተፋፈለ እቅድ፣ ሐማስ እ.አ.አ ታህሳስ 7 ባደረሰው ጥቃት የወሰዳቸው ታጋቾች እና በእስራኤል የተያዙ የፍልስጤም እስረኞች እንዲለቀቁ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እና ልሂቃንን የቀፈ የፍልስጤም መንግስት ተመስርቶ ከጦርነቱ በኃላ ጋዛን እንዲያስተዳድር ጠይቋል።

ሐማስ እና በእስራኤል ውስጥ እየተዋጋ መሆኑ የሚገለፀው እስላማዊው ጅሃድ ቡድንም እቅዱን መመልከታቸው ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የእስራኤል ጦር አርብ እለት በሰሜን፣ በማዕከላዊ እና በደቡብ ጋዛ ሐማስ ላይ ያነጣጠረ የአየር ድብደባ እና የምድር ዘመቻ ማካሄዱን ቀጥሏል። በማዕከላዊ ጋዛ የሚገኙት ኡሴይራት እና ማጋዚ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ለሊቱን መመታታቸውንም ነዋሪዎች ገልፀዋል። ቡሬጂ በተሰኘ ሌላ መጠለያ ጣቢያም ከፍተኛ ድብደባ መድረሱ ተገልጿል።

በተለይ በደቡባዊው ካሃን ዩኒስ ከተማ ከፍተኛ ውጊያ መካሄዱ የተገለፀ ሲሆን፣ ሐሙስ ማታ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ ያረፈ የእስራኤል ቦምብ ስምንት ፍልስጤማውያን መግደሉን የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተመሳሳይ የእስራኤል ታንኮች ቡሬጅ ከተማ አቅራቢያ የታዩ ሲሆን፣ ሐማስ የእስራኤልን ታንኮች እና ወታደሮች ኢላማ ሲያደርግ የሚያሳይ ምስል ለቋል። ሆኖም ሮይተርስ የምስሉን ትክክለኛነት ማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት በበኩሉ ባወጣው ሪፖርት፣ በጋዛ ሰርጥ የተጠናከረው ውጊያ፣ ተደጋጋሚ የመገናኛ መንገዶች መቆራረጥ፣ የመንገድ መዘጋት እና የነዳጅ እጥረት፣ በሰብዓዊ ተግባራት ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለሉ መሆኑን ገልጾ አስጠንቅቋል።

በሌላ በኩል በዌስት ባንክ፣ የእስራኤል ጦር፣ ሐማስን በገንዘብ ይረዱ ነበር በተባሉ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሐሙስ እለት ማካሄዱን ገልጿል። የእስራኤል መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ በዌስት ባንክ ባካሄደው ዘመቻ 21 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና በአስር ሚሊየኖች የሚቆጠር የእስራኤል ገንዘብ መያዙን አመልክቷል።

እስራኤል ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመሆን በአሸባሪነት የፈረጀችውን የሐማስ ቡድን ለማጥፋ ዘመቻዋን አጠናክራ በቀጠለችበት በዚህ ወቅት፣ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር መነጋገራቸው እና ከቀጠናው እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ዘላቂ ተኩስ አቁም ለማምጣት እንዲሰሩ ማሳሰባቸው ተዘግቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG