በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሐማስ ቅዳሜ የሚለቀቁ ታጋቾችን ስም ይፋ አደረገ


እስራኤላውያን ታጋቾች ያርደን ቢባስ፣ ኦፌር ካልዴሮን እና ኪት ሲጌል እአአ ከጥቅምት 7/2023 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ታስረው የነበሩ ናቸው፡፡
እስራኤላውያን ታጋቾች ያርደን ቢባስ፣ ኦፌር ካልዴሮን እና ኪት ሲጌል እአአ ከጥቅምት 7/2023 ጀምሮ በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ታስረው የነበሩ ናቸው፡፡

የሐማስ ታጣቂ ቡድን በመጪው ቅዳሜ የሚለቀቁ ታጋቾችን ስም ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ እስራኤልም እንደሚለቀቁ አረጋግጣለች። ለአራተኛ ዙር የሚደረገው የታጋቾች እና የእስረኛ ልውውጥ የሚካሄደው፣ ላለፉት 15 ወራት በጋዛ የተካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰውን የተኩስ ማቆም ስምምነት ተከትሎ ነው።

ቅዳሜ ከሚለቀቁት ታጋቾች መካከል እ.አ.አ በጥቅምት 7፣ 2023 በሐማስ በተፈጸመው ጥቃት ከባለቤቱ ሺሪ እና ከሁለት ወንዶች ልጆቹ ጋር የተወሰደው የ35 ዓመቱ ያርደን ቢባስ ይገኝበታል። የቤተሰቡ እጣ ፈንታ ግን እስካሁን አልታወቀም።

ሁለተኛው የሚለቀቀው ታጋች፣ በዩናይትድ ስቴትስ ኖርዝ ካሮላይና ግዛት የሚኖረው እና የአሜሪካ እና እስራኤል ጥምር ዜግነት ያለው የ65 አመቱ ኪትዝ ሲገል ሲሆን፣ እሱም ከባለቤቱ አቪቫ ሲገል ጋር ነበር የተወሰደው። ባለቤቱ አቪቫ ሲገል በሕዳር 2023 ተደርጎ በነበረው የተኩስ ማቆም ስምመንት ወቅት ተለቃለች።

ሦስተኛው ታጋች የፈረንሳይ እና እስራኤል ዜግነት ያለው የ54 አመቱ ኦፈር ካልደሮንም፣ አብረውት ታግተው የነበሩት ሁለት ህፃናት ልጆቹ እና ከቀድሞ ባለቤቱ በህዳር ወር ተለቀው ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የተኩስ ማቆም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ ባሉት ቀናት ከ423 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ወደ ሰሜናዊ ጋዛ መመለሳቸው ተገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG