በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዘንድሮው ሃጅ ተጀመረ


ከእስልምና አበይት አዕማደ ሥርዓት አንዱ የሆነው ሃጅ ዛሬ በሜካ፤ ሳውዲ አረብያ ተጀምሯል። የኮሮናቫይረስ መዛመት ባሳደረው ሥጋት ምክንያት ዘንድሮ የሃጅና ዑምራ ተጓዦች ቁጥር ከወትሮ ያነሰ እንደሆነ ተነግሯል።

በእስልምና እምነት አንድ ሙስሊም በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ ሜካ ሂዶ ሥርዓቱን እንዲያደርስና አረፋን ወይም ኢድ አል አድሃን እንዲያከብር የሚጠበቅበት ሲሆን በዚሁ መሠረትም በየዓመቱ ከሁለት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ምዕመናን ወደ ሜካ ይሄዳሉ።

በዚህ ዓመት ግን በኮቪድ 19 ምክንያት ሃገር አቋራጭ መንገደኞች እንዳይገቡ ሳዑዲ አረቢያ በማገዷ በሥርዓቱ ላይና ለኢዱም የሚገኙት አንድ ሺህ የሚሆኑ የሃገሪቱ ተወላጆችና ከሣምንታት በፊት የተመረጡ የውጭ ተወላጅ ነዋሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

በበአሉ ላይ የሚገኙት ዕድሜአቸው ከሃያ እስከ ሃምሣ ዓመት ባለው ክልል ውስጥ ያሉ ሲሆኑ ወደ ሜካ ከመሄዳቸው በፊት የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑ ተገልጿል። የሃጅ ሥርዓቱ ከመጀመሩ በፊትም፣ በየሆቴሎቻቸው ተወስነው እንዲቆዩ ተደርጓል።

ለአምስት ቀናት የሚዘልቀው ሥርዓትና ኢድ በኋላም ለአንድ ሣምንት ያህል ተለይተው ወይም ኳራንቲን ላይ ሆነው መቆየት ይጠበቅባቸዋል።

ሳውዲ አረብያ ከሁለት መቶ ሰባ ሺህ በላይ የኮቪድ 19 ህሙማን እንዳሏትና ወደ 2,800 የሚጠጋ ቁጥር ያለው ሰው በወረርሽኙ ምክንያት እንደሞተባት ታውቋል።

XS
SM
MD
LG