በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ትረምፕ “ስደተኞች ውሻና ድመት ይበላሉ” ማለታችው ሄይቲ አሜሪካውያንን ሥጋት ላይ ጥሏል


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት የሪፐብሊካን ፓርቲው እጩ ዶናልድ ትረምፕ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በተደረገው ፕሬዝደንታዊ ክርክር ላይ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት የሪፐብሊካን ፓርቲው እጩ ዶናልድ ትረምፕ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በተደረገው ፕሬዝደንታዊ ክርክር ላይ

የቀደሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በተደረገው ፕሬዝደንታዊ ክርክር ላይ “በኦሃዮ የሚገኙ ስደተኞች ለማዳ የቤት እንስሳት ይበላሉ” ሲሉ በሃሰትና ስም በሚያጠፋ መልኩ መወጀላቸውን ተከትሎ፣ ሄይቲ አሜሪካውያን ለደህንነታቸው ሥጋት እንደሚሰማቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።

በአሜሪካ የሚገኙ የሄይቲ አሜሪካውያን ማኅበረሰብ ተወካዮች እንዳሉት፣ የሪፐብሊካን ዕጩው ዶናልድ ትረምፕ፣ “በኦሃዮ ስደተኞች ለማዳ የቤት እንስሳት አርደው ይበላሉ” ሲሉ መናገራቸው ለሕይወታቸው አስጊ ሁኔታን እንደፈጠረና፣ ማኅበረሰቡ በብዛት በሚገኝባት ስፕሪንግፊልድ፣ ኦሃዮ ባሉ ነዋሪዎች ዘንድ ውጥረትን እንደፈጠረ አስታውቀዋል። ወደ ከተማዋ በቅርቡ የመጡ በሺሕ የሚቆጠሩ የሄይቲ ስደተኞች የአካባቢው ኢኮኖሚ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም፣ መንግሥት በሚያቀርባቸው አገልግልቶች ላይ ጫና መፍጠራቸው ተነግሯል።

ፕሬዝደንት ትረምፕ፣ “ውሾችን የበላሉ፣ ድመቶችንም እየበሉ ነው” ሲሉ በክርክር መድረኩ ላይ መናገራቸው፣ የፖለቲካ ሕይወታቸውን በተለይ የሚገልጸውና በስደተኞች ላይ በተደጋጋሚ የሚያሰሙት ሃሰተኛ ወሬ አካል መሆኑም ተነግሯል።

ከክርክሩ ቀደም ብሎም፣ በምክትል ፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት ጄ.ዲ. ቫንስ፣ በምክር ቤት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት፣ እንዲሁም ቢሊየኑሩ እና የ X ማኅበራዊ መድረክ ባለቤት ኢላን መስክ የሃሰት ወሬውን ሲያሰራጩ ሰንብተዋል።

የስፕሪንግፊልድ ከተማ ባለሥልጣናት እንዳሉት፣ ከሄይቲ የመጡት ስደተኞች፣ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሃገሪቱ የገቡና በአካባባው የሚገኙት ፋብሪካዎችና የሸቀጥ ማከፋፈያ መጋዘኖች የሥራ ዕድል ስላስገኙላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ስደተኞቹ የቤት እንስሳት ስለመብላታቸው የደረሳቸው አስተማማኝ ጥቆማ እንደሌለ አስታውቀዋል።

“ዘ ሄይሺያን ታይምስ” የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በስፕሪንግ ፊልድ የሚገኙት የሄይቲ ተወላጆች፣ ልጆቻቸውን ወደ ት/ቤት ከመላክ የተቆጠቡ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ዛቻ፣ ጥቃት እና የዘር ጥላቻ መልዕክቶች ቤታቸው ድረስ እየመጣ መሆኑን ምንጮች ለጋዜጣው ጥቆማ ማቅረባቸው ተነግሯል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG