በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር የኬንያ ፖሊስ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናገሩ


የሄይቲ ጠቅላይ ሚንስትር ጋሪ ኮኒል በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እአአ ሀምሌ 3/2024
የሄይቲ ጠቅላይ ሚንስትር ጋሪ ኮኒል በኒውዮርክ ከተማ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እአአ ሀምሌ 3/2024

የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር ጌሪ ኮኒል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ትላንት ረቡዕ ባደረጉት ንግግር፣ በቅርቡ በሀገራቸው የተሰማሩት የኬንያ ፖሊሶች የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር እና ወደ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማምራት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።

200 የኬንያ ፖሊሶችን ያካተተው የመጀመሪያው ዙር ተጠባባቂ ኃይል ፖርቶ ፕሪንስ የደረሰው ባለፈው ወር ሲሆን ፖሊሶቹ እስካሁን ያሳዩት ጠቀሜታ "እጅግ በጣም አዎንታዊ" መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

መንግሥታቸው የወሮበሎችን ጥቃትና የምግብ ዋስትና ችግር ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ለምክር ቤቱ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኮኒል፣ በሕገ መንግሥትና የፖሊስ ኅይል ማሻሻያዎች ነፃ ምርጫ እንደሚካሄድ በማረጋገጥ ሕዝቡ በፖሊስ ላይ ያለውን እምነት እንደገና እንደሚገነቡም ገልጸዋል።

ኬንያ ለዓለም አቀፉ የፖሊስ ኃይል 1 ሺህ ፖሊሶችን ለመላክ ቃል የገባች ሲሆን፣ ኮኒል ቀጣዩ ክፍለ ጦር "በቅርቡ" ይደርሳል ብለዋል። ከኬንያ በተጨማሪ የባሃማስ፣ ባንግላዲሽ፣ ባርቤዶስ፣ ቤኒን፣ ቻድ እና ጃማይካ ፖሊሶች በአጠቃላይ 2ሺህ 500 ይደርሳሉ ተብሎ የሚጠበቀውን የፖሊስ ኃይል ይቀላቀላሉ።

ሄይቲ የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመዋጋት የሚያስችላት ዓለም አቀፍ ኃይል እንዲመደብላት የጠየቀችው እ.አ.አ በ2022 ሲሆን ኬንያውያን ፈቃደኝነታቸውን ከማሳየታቸው በፊት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ አንድ ሀገር ኃይሉን እንዲመራ ሲማፀኑ ቆይተዋል።

እ.አ.አ በ2021 የሄይቲ ፕሬዝዳንት በነበሩት ጆቨኔል ሞይስ ላይ ግድያ ከተፈፀመ ወዲህ፣ እየተጠናከሩ የመጡት የተደራጁ ወንጀለኞች በአሁኑ ወቅት 80 ከመቶ የሚሆነውን የዋና ከተማ ክፍል ይቆጣጠራሉ ተብሎ ይገመታል። በወንበዴዎቹ የሚፈፀሙ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር እና አፈና እየተስፋፋ መሄድም ከፍተኛ አመፅ አስከትሏል።

በዓለም አቀፉ የፖሊስ ኃይል በመታገዝ ኮኒል እ.አ.አ በየካቲት 2026 እንዲካሄድ ለሚጠበቀው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጅት ሀገሪቱን የማረጋጋት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG