በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሐዲያ ዞን ሾኔ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች 697 መምህራን፣ ለወራት የተቋረጠባቸው ውዝፍ ደመወዝ እንደተከፈላቸው፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቁ። የምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ አስተዳዳር መምህራንም፣ ለወራት ተቋርጦባቸው የቆየው የደመወዝ ክፍያ፣ እየተቆራረጠም ቢኾን እንደተጀመረላቸው ተናግረዋል።
መምህራኑ፣ “ለወራት በከፍተኛ ችግር እና እንግልት ውስጥ አልፈናል፤” ሲሉ፣ ያለደመወዝ የከረሙበትን አዳጋች ኹኔታ ገልጸዋል። ከዚኽም በኋላ፣ ደመወዛቸው ወቅቱን ጠብቆ እንዲከፈላቸው ጠይቀው፣ ፍላጎታችን፥ “ሞያዊ ሓላፊነታችንን በአግባቡ መወጣት ነው፤” ብለዋል።
በጉዳዩ ላይ፣ የከተማ አስተዳደሩን፣ እንዲሁም የወረዳዎችንና የዞኑን ባለሥልጣናት አስተያየት ለማካተት ብንሞክርም፣ ስልካቸውን ስለማያነሡ አልተሳካም።
ይኹንና፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሓላፊ አቶ አንተነህ በፈቃዱ፣ ቀደም ሲል ከአሜሪካ ድምፅ ቀርቦላቸው ለነበረ ጥያቄ፣ ችግሩ በበጀት እጥረት እና በተያያዥ ምክንያቶች የተፈጠረ እንደኾነ ጠቅሰው ከዞኖቹ የሥራ ሓላፊዎች ጋራ እየመከሩበት እንደኾነ ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም