ማዕከላዊ ሶማሊያ በለድዌን ከተማ ውስጥ ታጣቂዎች ዛሬ ማክሰኞ የአገር ሽማግሌዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ስብሰባ ላይ የነበሩበትን ሆቴል ወረዋል። ሆቴሉ አሁንም በታጣቂዎቹ እንደተወረረ መሆኑን ዕማኞች እና ሆቴሉ ውስጥ ያሉት ሰዎች ቤተሰቦች ተናግረዋል።
የበለድዌን ከተማ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣን የሆኑት ዳሂር አሚን ጄሶው "እስከአሁን ባወቅነው መሠረት ቢያንስ አራት ሰዎች ተገድለዋል" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ፅንፈኛ እስላማዊው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ለጥቃቱ ኃላፊነት የወሰደ ሲኾን ከዐስር የሚበልጡ ሰዎች ገድለናል ብሏል።
አሊ ሱሊማን የተባሉ ባለመደብር "መጀመሪያ ኃይለኛ ፍንዳታ ሰማን። ከዚያም ተኩስ ቀጠለ። እንደገና ሌላ ፍንዳታ ተደገመ" ማለታቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል። ታጣቂዎቹ እና የመንግሥቱ ኃይሎች እየተታኮሱ ያሉበት ካሂራ ሆቴል በከፊል መፈራረሱን ዕማኙ አክለው ገልጸዋል።
ሆቴሉ አቅራቢያ የሚኖሩ ሀሊማ ኑር የተባሉ ሌላ ዕማኝ በበኩላቸው ሆቴሉ በታጣቂዎች እንደተወረረ መኾኑን እና አልፎ አልፎ ተኩስ እንደሚሰማ ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም