ሁለት የአይቮሪ ኮስት ከተሞች በወታደራዊ አመፅ ተውጠዋል፡፡
የአሁኑን ቁጣ ያነሱት ቀደም ስል የአማፂ ቡድን አባላት የነበሩና ጦራቸው ከተፈታ በኋላ ወደ ሃገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች እንዲቀላቀሉ የተደረጉ ወታደሮች ሲሆኑ የቀድሞ ትጥቃቸውን ሲፈቱ ይሰጣችኋል ተብለው የነበረ የጉርሻ ክፍያ እስከአሁን እንዳልተሰጣቸው ተገልጿል፡፡
የአይቮሪ ኮስት የምጣኔ ኃብት ማዕከል በሆነችው አቢዦን በርካታ ወታደራዊ ተቋማት ውስጥና ሁለተኛዪቱ ግዙፍ ከተማ ቡአኬ ውስጥ ዛሬ ተኩሶች መሰማታቸው ቢዘገብም የደረሰ ጉዳት ይኑር አይኑር ገና አልተገለፀም፡፡
ያመፁት ወታደሮች ቡአኬን የከትናንት በስተያው ዓርብ ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠሩ ሲሆን መንግሥቱ መልሶ ለመያዝ ጦር መላኩ ታውቋል፡፡
ትናንት - ዕሁድ በተካሄዱ የተኩስ ልውውጦች አንድ ሰው ሲገደል ሃያ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተሰምቷል፡፡
አማፂያኑ ትጥቅ የማስቀመጥ ሃሣብ እንደሌላቸውና የመንግሥቱን ወታደሮች ለመግጠም እየጠበቁ መሆናቸውን ከመካከላቸው አንዱ የሆነ ሃምሣ አለቃ ለሮይተርስ የዜና አውታር ተናግሯል፡፡
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ