በጊኒ፣ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ከተፈጸመባት በኋላ ሕይወቷ ባለፈው አንዲት ታካሚ ጋራ በተያያዘ የተከሠሡ የሕክምና ዶክተሮች፣ ጥፋተኛ ተብለው ወህኒ ወርደዋል፡፡ በሆስፒታል የተፈጸመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል፣ የአገሪቱን ሕዝብ ክፉኛ አስደንግጦ ሰንብቷል፡፡
“በጊኒ፣ በሆስፒታል ውስጥ የተደፈረችው የ25 ዓመቷ ታካሚ፣ ጸሓፊ መማ ሲላ፣ ከኹለት ዓመት በፊት፣ በቱኒዚያ በሕክምና በመረዳት ላይ ሳለች ሕይወቷ አልፏል፤” ሲል፣ መንግሥት በወቅቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡
በኮናክሪ የሚገኝ የወንጀል ችሎት፥ ዳንኤል ላማ፣ ፓትሪስ ላማ እና ሴለስቲን ሚሊሙኖ የተባሉ ሐኪሞች፣ ወጣቷን ጸሐፊ አስፈራርተው በፈጸሙባት የአስገድዶ መድፈር፥ ሕይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ እና በፅንስ ማስወረድ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ሴቦሪ ሲሴ የተባለ አራተኛ ሐኪም፣ ሌሎችን አደጋ ላይ በመጣል በሚል ጥፋተኛ ተብሏል፡፡
የወንጀል ችሎቱ፣ ጎጂ ንጥረ ነገር ለታካሚ መስጠት በሚል፣ አራቱ ሐኪሞች የተከሠሡበትን ወንጀል ውድቅ ተደርጓል፡፡
ዳንኤል ላማ እና ፓትሪስ ላማ እያንዳንዳቸው በ15 ዓመት እስራት ሲቀጡ፣ ሲሴ ደግሞ በአንድ ዓመት እስራት ተቀጥቷል፡፡ በሕግ ቁጥጥር ሥር ያልዋለውና እየተፈለገ ያለው ሚሊሙኖ ደግሞ፣ በ20 ዓመት እስራት ተቀጥቷል፡፡ በግለሰቡ ላይ የመያዣ ትእዛዝ እንደወጣበት የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል፡፡
የወጣቷ ጸሐፊ መማ ሲላን ሞት ተከትሎ፣ “ፍትሕ ለመማ ሲላ” የሚል ዘመቻ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲደረግ ቆይቷል፡፡