ዘንድሮ አሥረኛ ዓመቱን ያከበረው የኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ ውድድር ትናንት ሰላሣ አምስት ሺህ ህዝብ በማሳተፍ ተካሂዷል። የመሮጫ መሥመሩን የቀየሩትና በቤተ መንግሥት በኩል እንዳያልፍ የተደረገው በፖሊስ ስለተነገራቸው መሆኑን የውድድሩ አማካሪ ገልፀዋል።
በታዋቂው አትሌት በኃይሌ ገብረሥላሴ የተጀመረው የታላቁ ሩጫ ውድድር ሁሌም በዕድገት ላይ፣ ሁሌም ደማቅ ሆኖ መቀጠሉን አስመስክሯል። የተሳታፊዎቹ ቁጥር ከዓመት ወደዓመት እየጨመረ መምጣቱ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የዛሬ አሥር ዓመት ውድድሩ ሲጀመር ተሳታፊዎቹ አምስት ሽህ ብቻ ነበሩ፥ ዘንድሮ ሰላሣ አምስት ሺህ ደርሷል። ካሁን ቀደም የታላቁ ሩጫ ሥራ አስኪያጅ አሁን አማካሪ ሆነው እየሠሩ ያሉት ሪቻርድ ነሩርከር እንዳሉትም ከውጭ የሚመጣውም ተሳታፊ ቁጥር ጨምሯል።
አወዛጋቢውን የሺህ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሰባት ምርጫ ተከትሎ ሠልፎች ተከልክለው በነበሩባት ኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ የተቃውሞ ድምፅ ማሰሚያ የሆነባችው አጋጣሚዎች ታይተዋል። ከዚያ ምርጫ በኋላ በቀጠሉት ጥቂት ዓመታት መፈክሮች የሚያሰሙ፥ ተቃውሞአቸውን በዘፈንና በስንኝ ለመግለጽ የሚሞክሩ ተሳታፊዎችን ማየት አዲስ አልነበረም። የሩጫው መሥመር በብሔራዊው ቤተ መንግሥት የሚያልፍ መሆኑም በዚህ ሥፍራ ለሚሰሙ ድምፆች ምክንያት ሳይሆን አልቀረም። ዘንድሮ የሩጫው መሥመር ተቀይሯል። በቤተ መንግሥት ማለፉ ቀርቶም በመስቀል አደባባይ፥ ወደቄራና ወደጎተራ በመስቀል ፍላወር ወደኦሊምፒያ፥ ተመልሶ ወደመስቀል አደባባይ ሆኗል።
የመሮጫው መስመር የተቀየረውና በተለይም በቤተ መንግሥት በኩል እንዳያልፍ የተደረገው በሀገሪቱ ፖሊስ ስለተነገራቸው መሆኑን የዝግጅቱ አማካሪ ሪቻርድ ነሩርከር ለቪኦኤ ገልጠዋል።
ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ።