የሶቪየት ኅብረት የመጨረሻ ፕሬዚዳንት የነበሩትን የሚኻይል ጋርባቾቭን ዜና እረፍት ተከትሎ ከዓለም ዙሪያ የኀዘን መግለጫዎችና የተለያዩ መልዕክቶች እየወጡ ነው።
የሩሲያ ፕሬዚደንት ቭላዲሚር ፑቲን በጋርባቾቭ ህልፈት በጥልቅ ማዘናቸውን በቃል አቀባያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ገልፀዋል።
ያለፈው መቶ ክፍለዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጎልቶ የሚታወቅበት ቀዝቃዛው ጦርነት ደም ሳይፋሰስ እንዲያከትም በማድረጋቸው በብዙዎች ይሞገሳሉ።
በአንፃሩ ደግሞ የለውጥ እርምጃዎቻቸው ልዕለ ኃያል የነበረችውን ሶቪየት ኅብረትን ወደ መበተን በመውሰዱ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሩሲያዊያን ዘንድ ጠላት ተደርገው እንደሚታዩ ይነገራል።
በሚኻይል ጋርባቾቭ ማረፍ እጅግ ማዘናቸውን የገለፁት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ "የታሪክን አቅጣጫ የቀየሩ ልዩ መሪ" ሲሉ ገልፀዋቸዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄምስ ቤከር ደግሞ "ሚኻይል ጎርባቾቭን ታላቋን ሀገራቸውን ወደዴሞክራሲ በመሩ ታላቅ ሰውነታቸው በታሪክ ይታወሳሉ" ብለዋል።
ጋርባቾቭ ስላካሄዷቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሆነዋል።
የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም እንዲያከትም ጥሪ ያቀረቡትና የሃገራቸውና የዩናይትድ ስቴትስን ግንኙነቶች እንዲሻሻሉ ያደረጉት ጋርባቾቭ እአአ በ1987 ከወቅቱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ሮናልድ ሬጋን ጋር የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ኑክሌር ኃይሎች ስምምነትን ተፈራርመው በሺሆች የሚቆጠሩ አረሮችን በማስወገድ አውሮፓን ተደግኖባት ከነበረው አደጋ መታደጋቸውም ይነገርላቸዋል።
በቀደሙት የሶቪየት ህብረት መሪ በሊዮኒድ ብሬዥኔቭ ተጀምሮ ለአሥር ዓመታት የነበረውን የአፍጋኒስታን ጦርነት በ1989 ዓ.ም. አቁመዋል።
ጋርባቾቭ ዘጠና አንድ ዓመታቸውን የደፈኑት ባለፈው የካቲት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጦርነት ከመክፈቷ ከአንድ ሣምንት በፊት ሲሆን ህመም ላይ መቆየታቸው ተዘግቧል።