በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ በመንግስትና በፋኖ ቡድን ታጣቂዎች መካከል ትላንት በነበረው ግጭት ወደ ደባርቅ አጠቃላይ ሆስፒታል ቆስለው ከገቡት ውስጥ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ የሶስት አመት ህፃንን ጨምሮ 28 ሰዎች መቁሰላቸውን የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አስታውቀዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ አቶ አለ አምላክ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ ሲናገሩ ከሟቾቹ ውስጥ አንድ ታጣቂና አንድ ሲቪል ናቸው ብለዋል ::ወደ ሆስፒታል ሳይደርሱ የህፃኑን አባት ጨምሮ ከ7 በላይ ስዎች መሞታቸውን አክለው ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ በዳባት ከተማ ትላንት በነበረው ግጭት ከ6 በላይ ቤቶች በከባድ መሳሪያ ተመትተው መመልከታቸውን በወረዳው ፀጥታን ለማስከበር ስራ ሲዘዋወሩ እንደነበር የተናገሩት የጭላ ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ምናለ ግምብነህ ናቸው፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን በሁለቱ ወረዳዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ቢምረው ካሴ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ምክንያት ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡
የአማራ ፋኖ ጎንደር እዝ መምርያ አስተዳደር ሃላፊ መሆናቸውን የነገሩን አቶ አንተነህ ድረስ ግጭቶች መኖራቸውን ገልጸው “የፋኖ ታጣቂዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሱት ጉዳት የለም” ብለዋል፡፡
በጎንደር ከተማ ዙርያ ውጊያ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ አንተነህ ድረስ “የከተማዋን አብዛኛው ክፍል ተቆጣጥረናል” ሲሉም ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ድምጽ የፋኖ ቡድን ታጣቂዎች ጎንደር ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ተቆጣጥረናቸዋል ስላሏቸው ቦታዎች ከሌላ ገለልተኛ አካል ማረጋገጫ አላገኘም፡፡
በሰሜን ጎንደር ዞን ትላንትና ዛሬ በመንግስትና በፋኖ ቡድን ታጣቂዎች መካከል ያለውን ግጭት በተመለከተ እስካውን በመንግስት በኩል ምንም አይነት ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠም፡፡ የአሜሪካ ድምፅ ከመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ጽ/ቤት በጉዳይ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙክራ አልተሳካም፡፡
መድረክ / ፎረም