የሊቢያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሙስጠፋ አብደልጃሊል የጋዳፊን መገደል ትሪፖሊ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አረጋግጠዋል።
ዩናይትድ ስቴትስም ስለሞአመር ጋዳፊ መገደል ከሊቢያ ባለልጣናት ማረጋገጫ ማግኘቷን አስታውቃለች።
ደም የተነከረ የጋዳፊ አስከሬን መሬት ላይ ተንጋሎ እና የሽግግሩ መንግሥት ከበውት የሚያሳይ ቪዲዮ በዓለምአቀፍ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ተሠራጭቷል።
ጋዳፊ የስድሳ ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበሩ ።
የሞአመር ጋዳፊ መገደል ዜናን ተከትሎ በመላዋ ሊቢያ ፈንጠዝያ ሆኗል።
የሊቢያ የሽግግር መንግሥት ባለልስጣናት ጋዳፊ ሲርቲ ላይ በተካሄደ ውጊያ መገደላቸውን እንዳስታወቁ ለአርባ ዓመታት በገዟት ሀገር ሌሎች ከተሞችም ፈንጠዚያ ሆኗል።
ጋዳፊ ለሁለት ወራት ተሸሽገው ሲሳደዱ የቆዩበት ወቅት መደምደሙ ለብሔራዊ የሽግግር መንግሥቱ በሀገሪቱ ላይ ቁጥጥሩን የሚያጠናክርበት ምዕራፍ ከፍቶለታል።
የጋዳፊ መገደል ዜና የተሰማው የሽግግሩ አስተዳደር ተዋጊዎች ዛሬ ሐሙስ ማለዳ ሲርቲ ላይ አዲሱን የሊቢያ ሰንደቅ ዓላማ ከሰቀሉ በኋላ ነው። ከተማይቱን ለበርካታ ሣምንታት ሲያናጋት በከረመው የደፈጣ ተኩስና የከበድ መሣሪያ ድምፅ ቦታ ወደሰማይ በሚንጣጣ የደስታ መግለጫ ተኩስና የመኪና ክላክስ ተተክቷል።
የቀድሞው መሪ የትውልድ ከተማ ሲርቲ የተያዘችው የሽግግሩ ምክር ቤት ዋና ከተማይቱን ትሪፖሊን ከተቆጣጠረና ጋዳፊና ቤተሰባቸው ጥለው ከሸሹ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ ነው።
የሽግግሩ መንግሥት ወታደሮች ሲርቲ ላይ መክተው ሲዋጉላችው የነበሩትን የመጨረሻዎቹን ታማኞቻቸውን ደምስሰው ጋዳፊን ምድር ውስጥ ባለ ምሽግ ተደብቀው አግኝተው ተኩሰው እንደገደሏቸው ገልጠዋል።
ኔቶም ዛሬ የጦር አይሮፕላኖቹ ሁለት የደጋፊዎቻቸው ተሽከርካሪዎችን ሲርቲ ውስጥ ሲዘዋወሩ አግኝተው መትተዋቸዋል ብሏል፡፡
የሽግግሩ ተዋጊዎች ሙታኢስ የሚባለውን አንደኛውን የጋዳፊ ልጅ ይዘውታል የሚሉ ዘገባዎችም ከሲርቲ ወጥተዋል። ሳይፍ አል ኢስላም የሚባለው ሌላው ልጃቸው የት እንዳለ አይታወቅም፡፡ የሽግግሩ ባለሥልጣናት በሰፊው የሀገሪቱ በረሃ አንዱ ጋ ተደብቋል ነው የሚሉት።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን የጋዳፊን መገደል ዜና እንደሰሙ በሰጡት መግለጫ እንዲህ ብለዋል።
"የኮሎኔል ሞአመር ጋዳፊን ሞትና በሲርቲና በሌሎችም ከተሞች ጦርነት ማብቃቱን የሚናገረውን ዜና ሰማን፡፡ ይህ ቀን ለሊብያ ታሪካዊ የለውጥ ቀን መሆኑ እነሆ ግልፅ ሆነ፡፡ በመጭዎቹ ቀናት የደስታ ፈንጠዝያዎችን፣ ደግሞም ብዙ ላጡት የጥልቅ ኀዘን ዝክሮችን እናያለን፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ይህ የመጀመሪያው ምዕራፍ መጨረሻ ብቻ መሆኑን ዛሬውኑ እንገንዘብ፡፡ መጭው መንገድ ለሊብያና ለሕዝቧ አስቸጋሪና በፈተናዎች የተመላ እንደሚሆን እናስብ፡፡"
ዋና ፀሀፊ ባን ኪ ሙን አክለው ሊቢያውያን በዚህ ፈታኝ ወቅት በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ ሲያደርጉ "ሊብያዊያን የመጭውን ጊዜ ተስፋና ቃል በተግባር መጨበጥ የሚችሉት በአንድነትና በብሔራዊ ዕርቅ ብቻ ነው፡፡ በሁሉም ወገን ያሉ ተዋጊዎች ብረታቸውን በሰላም ማውረድ አለባቸው፡፡ አሁን ጊዜው የፈውስና የመልሶ ግንባታ ነው፡፡ ጊዜው የመንፈስ ብልፅግናና ቸርነት እንጂ የበቀል አይደለም" ብለዋል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት የሊቢያ ተልዕኮ በወደፊት ዕርምጃዋ ለመርዳት ዝግጁ መሆኑን ዋና ጸሐፊው ገልጠዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገሮች ሄደው ሊቢያ ውስጥ የነበሩ ሥራ ፈላጊዎች ከረጅምና ከባድ ጉዞ በኋላ ከደቡብ ሊቢያ ቻድ ገብተዋል።
አፍሪቃዊያኑ በመስከረም ወር ፍፃሜ በአስራ አምስት ከበድ መኪናዎች ተሣፍረው ከደቡቡዊቱ የሊቢያ ከተማ ሴብሃ እንደተነሱ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም) ገልጿል።
ሥራ ፍፈጋ ሊቢያ ውስጥ የነበሩት እነዚህ ሰዎች በመውጫ ጉዟቸው ወቅት ያጋጠሟቸ ከባድ መሣሪያ የታጠቁ ያላቸውን ሁሉ እንደዘረፏቸው ተናግረዋል። ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ አገሮች የሆኑ አፍሪቃዊያን ሠራተኞች ፀረ-ጋዳፊ በሆኑ ኃይሎች ጥቃት ሲደርስብን ነበር ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የማይገሬሽን ድርጅት (IOM) አፍሪቃዊያኑ ከአስራ ሁለት ልዩ ልዩ አገሮች፣ በብዛት ግን ከናይጄሪያና ቻድ እንደሆኑ ገልጿል።
ዘገባውን ያዳምጡ፡፡