በትግራይ ክልል፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ቢሮዎች በየደረጃው በመስበር እና ማኅተሞችን በመንጠቅ መንግሥትን የማውረድ ሥራ እየተሠራ ነው፤ ሲሉ ፕሬዘደንቱ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል።
በዐዲስ አበባ የሚገኙት አቶ ጌታቸው፣ ዛሬ ኀሙስ፣ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም. ረፋድ፣ በሸራተን ዐዲስ ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ አኹን በክልሉ ያለው ኹኔታ፣ "የፕሪቶርያውን ስምምነት የሚጥስና ከፍተኛ ግጭት የሚፈጥር ስለኾነ፣ የፌደራል መንግሥቱ ይህን የሚያስቆም ርምጃ መውሰድ አለበት፤” ብለዋል።
“በምክር ቤት ወይም በካቢኔ ደረጃ ተሰብስበን የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በይፋ ያቀረብነው ጥያቄ የለም፤” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ የፌደራል መንግሥቱ ከህወሓት ጋራ ያቋቋመውን ጊዜያዊ አስተዳደር የመታደግ ሓላፊነት እንዳለበት አመልክተዋል።
ይህ ማለት “ጦር አዝምቶ ጦርነት ይቀስቅስ ማለት አይደለም፤” ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ነገር ግን፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋራ በመኾን፣ አኹን በክልሉ ባለው ኹኔታ ምክንያት ጦርነት እንዳይፈጠር የሚያስችሉ ርምጃዎችን መውሰድ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ነው፤” ሲሉ አስረድተዋል።
ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፣ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ከኤርትራ መንግሥት ጋራ ግንኙነት ያላቸው አመራሮች ይኖሩ እንደኾነ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ "ግንኙነት ያላቸው የተወሰኑ ግን አደጋ መፍጠር የሚችሉ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች አሉ፤" ሲሉ ወንጅለዋል፡፡
በዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር የኾኑት አቶ ዐማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው፣ ዛሬ ማምሻውን ለብዙኀን መገናኛ በሰጡት መግለጫ፣ በአኹኑ ጊዜ በትግራይ ክልል እየተካሔደ ያለው፣ "በወረዳዎች እና በከተሞች የሕገ መንግሥት ማስከበር እንጂ፣ መፈንቅለ መንግሥት ተብሎ እየተገለጸ ያለው ስሕተት ነው፤" ሲሉ ክሱን ተከላክለዋል፡፡
ከኤርትራ መንግሥት ጋራ "ግንኙነት አለ፤" በሚል በአቶ ጌታቸው የቀረበውን ውንጀላ በተመለከተም፣ የኤርትራ መንግሥትን ጨምሮ ከማንኛውም የውጭ አካል ጋራ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ይኹን የፌደራል መንግሥቱን ለመጉዳት የተደረገ ግንኙነት የለም፤ ሲሉ አቶ ዐማኑኤል ምላሽ ሰጥተዋል።
መድረክ / ፎረም