በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
የአመራር ቀውስ ውስጥ የገባው ህወሓት 50ኛ ዓመቱን አከበረ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክብረ በዓል ዕቅዱን ሰረዘ

የአመራር ቀውስ ውስጥ የገባው ህወሓት 50ኛ ዓመቱን አከበረ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክብረ በዓል ዕቅዱን ሰረዘ


የአመራር ቀውስ ውስጥ የገባው ህወሓት 50ኛ ዓመቱን አከበረ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክብረ በዓል ዕቅዱን ሰረዘ
please wait
  • Auto
  • 240p
  • 360p
  • 480p
  • 720p
  • 1080p

No media source currently available

0:00 4:30 0:00
  • Auto
  • 240p
  • 360p
  • 480p
  • 720p
  • 1080p

የአመራር ቀውስ ውስጥ የገባው ህወሓት 50ኛ ዓመቱን አከበረ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክብረ በዓል ዕቅዱን ሰረዘ

ካለፈው ዓመት ነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ግልጽ በወጣ የፖለቲካ አመራሮች መከፋፈል ሳቢያ በድርጅታዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኘውና ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋራ ፍጥጫ ውስጥ የገባው ህወሓት፣ 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን፣ ዛሬ የካቲት 11 ቀን አክብሯል።

በአንጻሩ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ “የሕዝብን አንድነት ላለመበተን” በሚል፣ በመንግሥት የታቀደው የበዓሉ አከባበር መሰረዙን አስታውቋል።

የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በተገኙበት፣ ዛሬ ማክሰኞ በመቐለ ከተማ በተከናወነው የምሥረታ በዓሉ አከባበር ላይ፣ “የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አለመመለስ ወደ አላስፈላጊ ውጥረት የሚያስገባና የፕሪቶርያውን የሰላም ሰምምነትም አደጋ ላይ የሚጥል ነው፤” ብለዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም፣ ለትግራይ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችኹ መልእክት አስተላልፈዋል።

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) የደርግን ሥርዓት በመቃወም የትጥቅ ትግል የጀመረበት 50ኛ ዓመት፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚከበር ቢኾንም፣ የክልሉ ጊዝያዊ አስተዳደር ግን በአደባባይ አላከበረውም።

የፓርቲውን የምሥረታ በዓል አስመልክቶ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ፣ ነዋሪዎች በየቤታቸው እንዲያከብሩት ጥሪ አቅርቧል።

ይህም ኾኖ፣ የድርጅቱ 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል፣ በክልሉ ልዩ ልዩ ከተሞች እንዲሁም በመቐለ የ"ትግራይ ስታዲየም" ተከብሯል።

የህወሓት ሊቀ መንበር ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል በተገኙበት በመቐለ የትግራይ ስታዲየም በተከናወነው የበዓሉ አከባበር ላይ፦ የፓርቲው አባላት፣ ደጋፊዎች እና የቀድሞ ተዋጊዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ላይ ዶር. ደብረ ጽዮን እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ አለ ያሉት አደጋ በተጠና አኳኀንና በውይይት ካልተፈታ፣ "ትግራይ ትበተናለች፤ ሕዝቧም ይጠፋል፤" ሲሉ አስጠንቅቀዋል። አያይዘውም፣ "ይህ የጥፋት ደመና የሚቀለበሰው፣ ህወሓት እና የትግራይ የጸጥታ ኀይሎች ያሳለፉት ውሳኔ ወደ ተግባር ሲቀየር ነው፤" ብለዋል።

ዶክተር ደብረ ጽዮን በንግግራቸው፣ “የትግራይ ሕዘብ ባለፉት ቅርብ ዓመታት፣ በገዛ አገሩ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ተቆጥሯል፤” ብለዋል። በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት "አብዛኛው የክልሉ ሕዝብ ሰላም አግኝቷል፤" ቢሉም "ገና ያልተፈጸሙ" ተግባራት መኖራቸውንም አብራርተዋል። ሊቀ መንበሩ “ጠላት” ብለው በጠሯቸው ኀይሎች የተያዘ የክልሉ የአስተዳደር ወሰን እንዳለም አመልክተዋል።

“በሕዝባችን ላይ የተፈጸመውን እልቂት በተመለከተ የተጠያቂነት አሠራር ገና አልተጀመረም። በህወሓት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከልም ፖለቲካዊ ድርድር እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎችም በተደራጀ መልኩ አልተጀመረም። ከዚኽም አልፎ፣ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት የተደራደረውና የፈረመው ህወሓት፣ የተሰረዘው ሕጋዊ ሰውነቱ አልተመለሰም። ይህም ወደ አላስፈላጊ መሳሳብ የሚያስገባ በመኾኑ የሰላም ስምምነቱን አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር እየታየ ነው።”

ህወሓት በፕሮግራሙ ላይ ለውጥ ለማድረግ እንዳቀደ በንግግራቸው የጠቆሙት ሊቀ መንበሩ፣ ለዚኹ ማሻሻያ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ እየተሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ትላንት ሰኞ፣ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ክፍፍል በእርቅ ለመፍታት በተጀመረው እንቅስቃሴ መሠረት፣ የየካቲት 11 ቀን የምሥረታ በዓልን በጋራ ለማክበር እየተሠራ እንደነበረ ገልጿል።

ኾኖም፣ እርቀ ሰላምን በማውረድ አብሮ የመሥራት ጥረቱን በማደናቀፍ ግርግር እና ግጭት ለመፍጠር የሚደረግ እንቅስቃሴ እንዳለ መንግሥት ተገንዝቧል፤ ያለው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ፣ በዚኽም ሳቢያ የአደባባይ አከባበሩ በአስተዳደሩ በኩል ተሰርዟል፤ ሲል አስታውቋል። የክልሉ ሕዝብ የምሥረታ በዓሉን በየቤቱ እንዲያከብርም ጥሪ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው፣ በትግርኛ ቋንቋ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችኹ መልእክት፣ በመላው ኢትዮጵያ ነበረ ያሉትን ጭቆና ለመገርሰስ፣ የትግራይ ሕዘብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋራ በመኾን ለዴሞክራሲ እና ለእኩልነት በጠመንጃ ለመፋለም፣ የካቲት 11 ቀን ኣፈሙዝ አንሥቷል፤ ብለዋል። የትጥቅ ትግል የሚደገፍ እንኳ ባይኾንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የካቲት 11 ቀን የተጀመረው ትግል፣ ዴሞክራስያዊ ሥርዐትን ለመትከል፣ በአገር ውስጥ የሚፈጠር ልዩነትን በውይይት ለመፍታትና የትጥቅ ትግልን ለመዝጋት ያለመ ነበር፤ በማለት አስረድተዋል።

ይኹንና “ባለፉት ዓመታት ልዩነቶችን ለመፍታት የተከተልነው የግጭት መንገድ ግን፣ የየካቲት 11 ዓላማዎችን የሚፃረሩ ናቸው፤” ሲሉ የተቹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ከባድ ዋጋ ተከፍሎ ወደ ድርድር መቀረባችንም የሚደነቅ ነው፤” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚኹ መልእክታቸው፣ "አሁንም ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በአፈ ሙዝ ለመፍታት የመፈለግ ምልክቶች አሉ፤" በማለት ጠቁመዋል። ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ተፈናቃዮች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በማድረግ፣ የልማት ሥራዎችን በማጠናከር፣ የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ የመልሶ ግንባታ ሥራዎችን ለመፈጸም፣ የተመረጠ መንግሥት እንዲመሠረትም አብረን እንሥራ፤" በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG