በጀርመን በገና ገበያ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እና በየካቲት ወር የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ተከትሎ፣ በድንበር ዙሪያ የሚካሄደው ቁጥጥር እንደ አውሮፓውያን የቀን አቆጣጠር ከመጪው መጋቢት 2025 ዓ.ም በኋላም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሀገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
ነሐሴ ወር ላይ አንድ ጅሃዲስት ነው ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ በቢላዋ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ፣ ሕገወጥ ስደትን ለማስቆም፣ በርሊን ከዘጠኝ ጎረቤት ሀገራት ጋራ በመተባበር ለስድስት ወራት የሚቆይ የድንበር ቁጥጥር መስከረም ላይ አውጃ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ወዲህም ወደ 1ሺህ 800 የሚኾኑ ሰዎች የታሰሩ ሲሆን፣ 40ሺሕ የሚሆኑ ወደ ጀርመን ሊገቡ የሞከሩ ሰዎች ደግሞ ወደመጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ናንሲ ፋዘል ለሀገር ውስጥ ጋዜጣ ተናግረዋል።
ከአውሮፓ ትልቁን ኢኮኖሚ የያዘችው ጀርመን ቀደም ሲልም ከኦስትሪያ፣ ፖላንድ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ስዊዘርላንድ ጋራ ለበርካታ ዓመታት የቆየ የድንበር ቁጥጥር ስምምነት የነበራት ሲሆን፣ ከመስከረም ወዲህ ደግሞ ከፈንሳይ፣ ሉክዘምበርግ፣ ቤልጂየም፣ ኔዘርላንድ እና ዴንማሪክ ጋራ በመተባበር ድንበር ላይ የቁጥጥር ማዕከላት አቋቁማለች።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ውድቅ የተደረጉ የጥገኝነት መጠየቂያ ማመልከቻዎችም ከ50 በመቶ በላይ መጨመራቸውም ተመልክቷል።
የጀርመን መንግስት ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ የመሰረቱት መንግሥት በኅዳር ወር መፍረሱን ተከትሎ በየካቲት ወር ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን፣ የጸጥታ እና የስደተኞች ጉዳይ የምርጫው ቁልፍ ጉዳይ መሆናቸው ተመልክቷል።
መድረክ / ፎረም