በአይሁድ ላይ የተፈፀመውን ፍጅት “ያሳነሰ” ያሉት የፍልስጥዔም ፕሬዚዳንት ንግግር እንዳስከፋቸው የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ገልፀዋል።
ፍልስጥዔማዊያን ታጣቂዎች በምዩኒክ ኦሊምፒክ በእሥራዔላውያን ላይ ጥቃት ያደረሱበት ሃምሣኛ ዓመት መታሰቢያ እየተቃረበ ሲሆን ትናንት፤ ማክሰኞ በርሊን ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት የፍልስጥዔሙ መሪ ማህሙድ አባስ ሲመልሱ “እሥራኤል /እአአ/ ከ1947 ዓ.ም. አንስቶ ስትገድል ቆይታለች” ብለዋል።
"እስራዔል በፍልስጥዔማዊያን መንደሮችና ከተሞች ሃምሣ ጭፍጨፋዎችን ፈፅማለች፥ ዴር ያሲን፥ ታንቱራ፥ ካፍር ካሲምና በሌሎችም ብዙ ቦታዎች ሃምሣ ጭፈጨፋዎችን፣ ሃምሣ *ሆሎኮስቶችን* ፈጽማለች" ብለዋል አባስ።
የፍልስጥዔሙ ፕሬዚዳንት ይህንን ያሉት ከጀርመን ቻንስለር ሾልዝ ጋር ሆነው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ ነበር።
የጀርመኑ ቻንስለር ዛሬ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት ፅሁፍ "የአባስ ንግግር እጅግ አስከፍቶኛል" ብለዋል።
"በተለይ በእኛ በጀርመኖች ዘንድ አምሳያ የለሹን የአይሁድ ጭፍጨፋ ለሌላ ማነፃፀሪያ ማድረግ ተቀባይነት የለውም፤ የተፈፀመውን ወንጀል ለማስተባበል የሚደረግ ማናቸውንም ሙከራ አወግዛለሁ" ብለዋል።
የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ያዪር ላፒድ ደግሞ "የአባስ አስተያየት የሞራል ውድቀት ብቻ ሳይሆን የለየለት ውሸት ነው፤ ታሪክ ይቅር አይላቸውም" ብለዋል።
** [“ሆሎከስት”፡- እአአ ከ1941 እስከ 1945 ዓ.ም. በተካሄደው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ናዚ ጀርመንና ተባባሪዎቿ በያዟቸው የአውሮፓ ግዛቶች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ስድስት ሚሊየን የሚሆኑ አይሁድን ዘር ለይተው በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ የፈጁበት ዘመቻ ነው።]