በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጀርመናዊያኑ ቱሪስቶች ተለቀቁ


በኢትዮጵያ አፋር ክልል ውስጥ ኤርታ-አሌ አካባቢ ባለፈው ጥር ዘጠኝ ቀን የተጠለፉትን ሁለት ጀርመናዊያን ሃገር ጎብኝዎች መልቀቁን አርዱፍ በሚል ምሕፃር የሚታወቀው የአፋር አማፂ ቡድን አስታወቀ፡፡

ሌሎች አምስት ሰዎች በተገደሉበት ድንገተኛ ጥቃት የተያዙትንና ከአንድ ወር ተኩል በላይ በቁጥጥሩ ሥር የቆዩትን እነዚህን ጀርመናዊያን አርዱፍ ባወጣው መግለጫ ይቅርታ መጠየቁን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡

የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዩኒት ግንባር - አርዱፍ ሁለቱን ጀርመናዊያን ለአካባቢው የሃገር ሽማግሌዎች ማስረከቡንም ገልጿል፡፡

የፈረንሣዩ የዜና አውታር አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዛሬ ባወጣው ዘገባ ደግሞ የጀርመን ኤምባሲ ባለሥልጣናትም ሁለቱን ጀርመናዊያን ከሃገር ሽማግሌዎቹ ጋር በአንድ የአፋር ምድረ በዳ ተገኝተው መረከባቸውን አመልክቷል፡፡

ተጠላፊዎቹ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ከዓለም እጅግ ሞቃት ሥፍራዎች አንዱ ነው በሚባለው አካባቢ እጅግ በከበደ በረሃማ የአየር ንብረት ውስጥ መቆየታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአካባቢው ለመንቀሣቀስ እንዳይቻል በማድረጉ ምክንያት ታጋቾቹን ቀደም ብለው ለማስረከብ ሣይመቻቸው መቅረቱን አማፂያኑ መግለፃቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

ከኢትዮጵያና ከጀርመን መንግሥታት የተሰጠ መግለጫ ወይም የተገኘ መረጃ ባይኖርም ቪኦኤ ባደረገው ጥረት ስለሁኔታው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ቅርበት ሊኖራቸው ይችላል የተባሉ የአካባቢው ሽማግሌዎች ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው፤ ለጊዜው ያገኘናቸው ባለሥልጣን መልሰው እንደሚደውሉልን ቃል ገብተው ለዜናው ወደስቱዲዮ እስከገባንበት ደቂቃ አልደወሉም፡፡ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡

XS
SM
MD
LG