የጀርመኑ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኢራን በእስራኤል ላይ ያደረሰቸውን መጠነ ሰፊ የሚሳይል ጥቃት በመደገፍ ትላንት ምሽት በርሊን ውስጥ የተካሄደውን የጸረ እስራኤል ተቃውሞ ሰልፍ በማውገዝ ዛሬ ረቡዕ የተሰማቸውን ቁጣ ገለጹ፡፡
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ናንሲ ፌዘር ፣ በኢራን ይታገዛሉ የተባሉትን ሁለቱን የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ እና የሊባኖስ ሂዝቦላህን በሚደግፉ ሰልፎች ላይ ፖሊስ እርምጃ ይወስዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ቴህራን ትላንት ማክሰኞ ማምሻውን እስራኤል ላይ 200 ሚሳይሎችን በመተኮስ ቀጥተኛ ጥቃት ከሰነዘረች በኋላ በርካታ ሰዎች ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ በርሊን ጎዳናዎች መውጣታቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
ፌዘር "እንዲህ አይነቱን ጥቃት በደስታ መደገፉ በጣም አስደንግጦኛል፣ አበሳጭቶኛልም” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሯ አያይዘውም "በጀርመን ውስጥ ሀማስን ወይም ሂዝቦላህን የሚያወድስ እና የሚደግፍ ማንኛውም ድርጊት በጎዳና ላይ እንኳ ቢሆን ያስቀጣል" ብለዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት እየተባባሰ በመሄዱ “በጀርመን ደህንነት ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ሁኔታ” የጸጥታ ክፍሉ በቅርበት ሲከታተለው ነበር” ሲሉም ፌዘር ተናግረዋል፡፡
“በእስላምና አክራሪዎች፣ ጸረ ሴማውያን እና ጸረ እስራኤል ድርጊቶች የተደቀነው አደጋ ከፍተኛ ነው” ያሉት ሚኒስትሯ “በተለይ በእስልምና አክራሪነት ውስጥ ባሉ ሰዎች ዘንድ ጽንፈኝነትና ስሜታዊነት የማየሉን ውጤት ከወዲሁ በጎዳናዎች ላይ ስላየነው” አውቀነዋል ብለዋል፡፡
እስራኤል ላይ በተፈጸመው የኢራን ጥቃት ደስታቸውን ለመግለጽ በበርሊን ጎዳናዎች የወጡ በርካታ ሰዎች የፍስልጤምን ስካርፍ ሲያደርጉ፣ ሌሎቹ የሊባኖስን ባንዲራ በማለውለብለብ “እንመክት!” እና “አላህ አክበር” (እግዚብአሄር ታላቅ ነው!) የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙ እንደነበር ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡
መድረክ / ፎረም