የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ኸርበርት ዋከር ቡሽ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
በቤተሰባቸው ቃል አቀባይ መግለጫ መሠረት በፓርኪንሰንስና ሌሎች ህመም ምክንያት በፅኑ ታመው ለብዙ ዓመታት በሆስፒታል ክትትል ሲደረግላቸው የቆዩት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት ቡሽ ትላንት ማታ ያረፉት ሂዩስተን ቴክሳስ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ነው። ጆርጅ ደብሊው ቡሽ እአአ ከ1989 እስከ 1993 ድረስ የዩናይትድ ስቴትስን የመሩ 41 ኛው ፕሬዚዳንት ነበሩ።
በእአአ 1989 መሪ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ኸርበርት ዋከር ቡሽ፡ በዓለሙና በአሜሪካ ፖለቲካ መድረክ በምርጫዎች ሲወድቁና ሲነሱ ቆይተዋል። በርሳቸው አመራር ወቅት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እየወደቀ በመምጣቱና የሥራ አጡ ቁጥር በመብዛቱ በ1992 ዳግም ተመርጠው ወደ ኃይት ሃውስ ለመግባት ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም። በምርጫው ተሸንፈው ወጥተዋል።
በፕሬዘዳንትነት በቆዩባቸው 4 ዓመታት ሚስተር ቡሽ በፓናማ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ አዘው በወቅቱ የነበሩትን አምባገነን መሪ ማኑኤል ኖሪዬጋን ከሥልጣን አባረዋል። ኋላም የኢራቁ መሪ ሳዳም ሁሴን በነዳጅ ዘይት ሃብታሟ ኩዌት ላይ ወረራ እንዳያካሂዱ ለመከላከል ጦርነት መክፈታቸው ይታወሳል።
ጆርጅ ደብሊው ኸርበርት ዋከር ቡሽ ሃገራቸውን ማገልገል የጀመሩት በወጣትነት ዕድሜያቸው ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የባህር ኃይል ተዋጊ ጄት በማብረር የጃፓን ዒላማዎችን ደብድበዋል። ያኔ ገና የ18 ዓመት ወጣት ነበሩ።
ፕሬዘዳንት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊትም በተለያዩ ቁልፍ ሥልጣኖች አገልግለዋል።
· በ1970 የመጀመሪያ ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር
· ጥቂት ቆየት ብሎም የሪፖብሊካን ፓርቲው ብሄራዊ ኮሚቴ ሊቀ መንበር
· በዚያኑ ዓመት በቻይና የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳዳርና
· የአሜሪካ የደኅንነት ጥበቃ ዋና መሥሪያ ቤት /የሲአኤ/ ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ኸርበርት ዋከር ቡሽ በወጣትነት ዕድሜ ከተዋወቋቸው ባለቤታቸው ባርባራ ቡሽ ጋር ለ73 ዓመታት በትዳር ቆይተዋል። ባርባራ ቡሽም በ92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ባለፈው ሚያዝያ መሆኑ ይታወሳል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ