ሄይቲ ውስጥ እየጨመረ በመጣው የተደራጁ የወሮበሎች ቡድን ጥቃት፤ ባለፈው የአውሮፓውያን 2024 ከ5 ሺሕ 600 በላይ ሰዎች መሞታቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዛሬ ማክሰኞ በአወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም መጎዳታቸውን እና መታገታቸውን አክሎ አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኃላፊ ቮልከር ተርክ በሰጡት መግለጫ "እነዚህ አሃዞች ብቻቸውን በሄይቲ እየተፈጸሙ ያሉትን ፍፁም ዘግናኝ ድርጊቶች ሊያመላክቱ አይችሉም” ብለው “ነገር ግን ሰዎች እየደረሰባቸው ያለውን የማያቋርጥ ጥቃት ያሳያሉ” ብለዋል።
ምንም እንኳን በዩናይትድ ስቴትስ እና በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የኬንያ የፖሊስ የድጋፍ ተልዕኮ በሂይቲ ድጋፉን ቢቀጥልም ሁከቱ ቀጥሏል። ዛሬ ማክሰኞ የወጣው መግለጫ "በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ በዋና ከተማዋ ፖርት ኦ ፕሪንስ ሲት ሶሌ አካባቢ በዋናው የወንበዴ ቡድን መሪ ዋርፍ ጄርሚ በተቀነባበረ ጥቃት በትንሹ 207 ሰዎች ተገድለዋል" ብሏል።
በጎርጎርሳውያኑ 2024 የመንግሥታቱ ድርጅት የመብት ቢሮ 315 የሚደርሱ እና "የወንበዴ ቡድን አባል ናቸው" የተባሉ ሰዎች ከሕግ አግባብ ውጭ መገደላቸውን መመዝገቡን አስታውቆ፤ አንዳንዴም ሁኔታው በሄይቲ ፖሊስ መኮንኖች አመቻችነት መፈጸሙንም አስፍሯል፡፡ በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ልዩ የፖሊስ አካላትን እንደተሳተፉባቸው የተጠረጠሩ 281 ክሶች መኖራቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።
"በሄይቲ በሰብአዊ መብት ረገጣ እና ጥሰቶች እና በደሎች ጥፋት ያለመከሰስ፣ እንዲሁም ሙስና ለረዥም ጊዜ መቀጠላቸው ግልጽ ሆኗል" በማለት የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ኃላፊው ቮልከር ተርክ ተናግረዋል።
የሀገሪቱ የፖሊስ ኃይል በዓለም አቀፍ ርዳታ በመብት ረገጣ የተጠረጠሩ ፖሊሶችን ተጠያቂ እንዲያደርግ ተርክ ጠይቀዋል።
"ወደ ሄይቲ የሚገቡ የጦር መሳሪያዎች ብዙውን ጊዜ በአሳዛኝ ሁኔታ በወንጀለኞች ቡድን እጅ ይወድቃሉ፡፡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፡፡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶች እና አገልግሎቶች፣ እንደ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች፣ ተረብሸዋል እንዲሁም ወድመዋል" ብለዋል፡፡ ተርክ በፀጥታው ምክር ቤት የሚጣለው ማዕቀብ እና የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንዲሆንም አሳስበዋል።
አክለውም የሄይቲ ዜጎች እንዲመለሱ የማድረጉ ሁኔታ መቀጠሉን ገልጸው የተቃወሙ ሲሆን “በሀገሪቱ ያለው ከፍተኛ የፀጥታ ችግር እና ያስከተለው የሰብአዊ መብት ቀውስ የሄይቲ ዜጎች በሰላም፣ በክብር እና በዘላቂነት እንዲመለሱ አይፈቅድም” ብለዋል።
መድረክ / ፎረም