ቃል አቀባዩ ማዪ ፋቲ ለፈረንሣይ የዜና ወኪል በሠጡት ቃል “የጃሜ የሥልጣን ዘመን ጥር 11 ይጠናቀቃል፤ የተመራጩ ፕሬዚዳንት ባሮ ዘመን ይጀምራል። ያንን የሚለውጥ አንዳች ነገር አይኖርም። በዚያው ቀን ያለ አንዳች ማስተጓጎል ቃለ-መሃላ ፈፅመው ሥራውን ይረከባሉ” ብለዋል።
የምዕራብ አፍሪካ ሃገሮች የምጣኔ ኃብት ማኅበር /ኤኮዋስ/ ተሰናባቹን ፕሬዚዳንት የኽያ ጃሜንና ተመራጩን አዳማ ባሮን ለማሸማገል ያደረገው ጥረት በመክሸፉ ሚስተር ባሮ ባለፈው ዕኩለ-ሌሊት ላይ ወደ ጎረቤት ሴኔጎል መሸሻቸውን ቃል አቀባዩ አመልክተዋል።
ባሮ ወደ ዳካር የሄዱት ለጥቃት የተጋለጡ በመሆናቸውና ለደህንነታቸው በመሥጋት መሆኑም ተገልጿል።
የሴኔጎል ፕሬዚዳንት ሚስተር ባሮን ለማስተናገድ ፍቃደኛ መሆናቸውም ታውቋል።
የፊታችን ሐሙስ ጥር 11/2009 ዓ.ም. ይፈፅማል የተባለውን ቃለ መሃላ የሚመሩት የኤኮዋስ የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት የላይቤርያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እንደሚሆኑ ተዘግቧል።