በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጋምቤላ አንድ ሰው ተደብድቦ ተገደለ


የክልሉ ፕሬዝደንት ጠባቂዎች ድብደባውን እንዳደረሱ የሟች ወገኖች ተናግረዋል

በጋምቤላ ክልል አንድ ሰው በክልሉ ፕሬዝደንት ጠባቂዎች እጅ መገደሉን ሟቹን በቅርብ የሚያውቁና የአካባቢው ተወላጆች እንደሆኑ የሚናገሩ ሰዎች ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

ሰኞ ምሽት ወደ አራት ሰአት ገደማ ላይ በድብደባ ህይወቱ ያለፈው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ግድያ ከምርጫ ጋር የተያያዘ አይደለም። የሟቹን ማንነት በቅርብ እንደሚያውቁት የነገሩንና ሙሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ፔንርያት የተባሉ ሰው ሲያብራሩ “አቶ ኡችዶ ኡዶላ ኦርየት የሚባል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማስተርስ የተመረቀ የአኝዋክ ተወላጅ ነው። በቢ.ፒ.አር ሰልጥኖ በአመቻችነት ይሰራ ነበር።

ኡችዶ ኡዶላ ኦርየት የተገደለው በክልሉ ፕሬዝደንት ኦመድ ቦንግ 4 ጠባቂዎች ተደብድቦ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ ኦማት የተባሉ የጋንቤላ ነዋሪ ናቸው። ሟች መብራት ጠፍቶ ነበርና እቃ ሊገዛ በሄደበት ጊዜ የፕሬዝደንቱ አራት ጠባቂዎች እግኝተው ደብድበው ገድለውታል ሲሉ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል ፕሬዝደንት ኦመዱ ቦንግ በግለሰቡ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ጉዳዩ በፖሊስ ማጣራት እየተደረገበት መሆኑን አብራርተዋል። ከዚያ በተለየ ግን የሚወሩ ወሬዎች የፈጠራ አሉባልታዎች እንደሆኑ ፕሬዝደንት ኦመዱ አስረድተዋል።

ሟቹ ድብደባው ከደረሰበት በኋላ ለቤተሰቡ ማን እንደደበደበው ተናግሯል። የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ የተማሩና ከክልሉ መንግስት ጋር የማይስማሙ ሰዎች ደብዛቸው እንደሚጠፋና በይፋ እንደሚገደሉ ይናገራሉ።

የክልሉ ፕሬዝደንት ኦመዱ ቦንግ ግን በጋምቤላ አንጻራዊ ሰላም መኖሩንና በተወሰኑ ግለሰቦች ላይ የተነጣጠረ ጥቃት የለም ይላሉ። በጋምቤላ ክልል በዚህ በምርጫ አመት የጸጥታ ችግር አለመታየቱን የክልሉ ባለስልጣናት ይገልጻሉ። ከዚህ በፊት በክልሉ የደረሱ የጅምላ ግድያዎችን የሰብ-አዊ መብት ድርጅቶች ያወገዙ ሲሆን አንዳንዶች “የዘር ማጥፋት” ነው እስከማለትም ደርሰዋል።

(የሬድዮ ዘገባውን በገጹ በስተቀኝ አምድ ማግኘት ይቻላል)

XS
SM
MD
LG