በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከወር በፊት ከታገቱት 12 ሕፃናት 8ቱ መመለሳቸውን የጋምቤላ ክልል አስታወቀ


ከወር በፊት ከታገቱት 12 ሕፃናት 8ቱ መመለሳቸውን የጋምቤላ ክልል አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:31 0:00

ከወር በፊት ከታገቱት 12 ሕፃናት 8ቱ መመለሳቸውን የጋምቤላ ክልል አስታወቀ

በጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ፣ ከአንድ ወር በፊት በታጣቂዎች ተፈጸመ በተባለ ጥቃት፣ 51 ሰዎች መገደላቸውንና 12 ሕፃናት ታግተው መወሰዳቸውን የገለጸው የወረዳው አስተዳደር፣ ከታገቱት ሕፃናት እስከ አሁን ስምንቱ መመለሳቸውን አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም፣ በጥቃቱ የሰዎች ሕይወት ማለፉንና የንብረት ጉዳት ማጋጠሙን የሚያሳዩ መረጃዎች ደርሰውኛል፤ ጉዳዩን ማጣራት ጀምሬአለኹ፤ ብሏል፡፡ ከግጭቱ ጋራ በተያያዘ የተፈናቀሉ 6ሺሕ100 ሰዎች፣ በቂ ርዳታ እየደረሳቸው እንዳልኾነ፣ የጆር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዑመድ ኡባንግ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ያለው የትራንስፖርት ችግር፣ በሰብአዊ ርዳታ ስርጭት ላይ ዕንቅፋት መፍጠሩን አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ቢሮ በበኩሉ፣ እስከ አሁን ድረስ ለተፈናቃዮቹ የምግብ ርዳታ እየቀረበ መኾኑን ገልጾ፣ ምግብ ነክ ያልኾኑ ድጋፎች ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚደርሳቸው ጠቁሟል፡፡

ባለፈው መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በጋምቤላ ክልል በጆር ወረዳ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት፣ 736 ቤቶች መቃጠላቸውንና 6ሺሕ100 ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ የክልሉ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል፡፡

የጆር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ዑመድ ኡባንግ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ በጥቃቱ ታግተው የተወሰዱ ሕፃናትም እንደነበሩ አስታውሰው፣ እስከ አሁን በተደረገ ጥረት የተወሰኑትን ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

የጋምቤላ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋድቤል ሙን ደግሞ፣ በጥቃቱ የሰዎች ሕይወት ማለፉን አውስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የጋምቤላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አቤል አዳነ በበኩላቸው፣ ከአንድ ወር ገደማ በፊት በተፈጸመው ጥቃት የደረሰውን ጉዳት እያጣራን ነው፤ ብለዋል፡፡

ከተባለው የታጣቂዎች ጥቃት ጋራ በተያያዘ የተፈናቀሉት 6ሺሕ100 ሰዎች በቂ ርዳታ እያገኙ እንዳልኾነ፣ በአኙዋ ዞን የጆር ወረዳ አስተዳዳሪው አቶ ዑመድ ኡባንግ ይናገራሉ፡፡ የሚመጣውን ርዳታ ለተረጅዎች ለማድረስም የትራንስፖርት ችግር መኖሩን ያመለክታሉ፡፡

የጋምቤላ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋድቤል ሙን በበኩላቸው፣ ለተፈናቃዮቹ፣ በሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ የምግብ እና ሌሎች ድጋፎች እንደቀረቡላቸው አስታውቀዋል፡፡

በየብስ ትራንስፖርት ተደራሽ ላልኾኑ ተረጂዎች፣ ርዳታውን በሞተር ጀልባ ለማድረስ የነዳጅ እጥረት መኖሩን የገለጹት አቶ ጋድቤል፣ የዚህ ምክንያቱ በክልሉም ተመሳሳይ ችግር በመኖሩ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ ምግብ ነክ ያልኾኑ ሌሎች ቁሳቁሶች ግን በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚደርሳቸው ጠቁመዋል፡፡

ለጋምቤላ ክልል ተፈናቃዮች በቂ ርዳታ አለመድረሱን የተናገሩት አቶ ጋድቤል ሙን፣ በተለይ መጪው ጊዜ የክረምት ወቅት መኾኑን ጠቅሰው፣ ተፈናቃዮቹ፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልኾኑ ድርጅቶች የበለጠ እገዛ እንደሚሹ አመልክተዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG