በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ስምንቱ ከበርቴ ሃገሮች ለአፍሪካ የምግብ ዋስትና አዲስ ዕቅድ ይፋ አደረጉ


የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በ ጂ8 ስብሰባ ላይ መገኘት አስመልክቶ ኢትዮጵያዊያን በዋሽንግተን የድጋፍና የተቃውሞ ሠልፍ አደረጉ፡፡

በኢንዱስትሪ የበለፀጉት የጂ8 አገሮች መሪዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ካምፕ ዴቪድ - ሜሪላንድ ላይ ሊመክሩ ከያዙት የነገው ቀጠሯቸው ቀደም ብሎ ዛሬ ውሏቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ቅድመ-ውይይት ተቀምጠዋል።

በዛሬው ውይይት አፍሪካን ወክለው የሚገኙት የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርና የቤኒን ፕሬዝደንት ያያ ቦኒ፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የታንዛኒያው ጃካያ ኪክዌቴና የጋናው ጆን አታ ሚልስ በድርቅ፣ በረሃብና በምግብ እጥረት ለተጎዱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ይበጃል ያሏቸውን ሃሳቦች ከፖሊሲ አውጭዎች ጋር መክረዋል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የዛሬውን ጉባዔ በውይይት ከፍተዋል።

በዚሁ በስምንቱ ከበርቴ ሃገሮችና ሌሎችም መሪዎች ስብሰባ ላይ አዲስ ዕቅድ ይፋ ተደርጓል፡፡

በስብሰባው ላይ ከሌሎችም የአፍሪካ መሪዎች ጋር የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የተገኙ ሲሆን ሲምፖዚየሙን በንግግር የከፈቱት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በማለም በሮናልድ ሬገን የዓለምአቀፍ ንግድ ማዕከል ሲካሄድ በዋለው ጉባዔ ፊት ለፊት ኢትዮጵያዊያን በድጋፍና በተቃውሞ ተሣትፈዋል።
“መለስ ዜናዊ የአፍሪካ መሪ የአገር አልሚ” ከሚሉ መፈክሮች አንስቶ “መለስ ዜናዊ መብት ረጋጭ አምባገነን” የሚሉ ተቃውሞዎችም ተሰምተዋል።

በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ያላቸው ሠልፈኞች የድጋፍና የተቃውሞ ድምፃቸውን ያሰሙት በሬገን ህንፃ ፊትለፊት ማለዳ ፀሐይ ሳትወጣ ጀምሮ ሲሆን እንዳይጋጩ በማሰብ ፖሲስ መሃላቸው ቆሞ ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ውስጥ በልማት ስም ይካሄዳል ያለው የውጭ ባለሃብቶች መጠነ-ሰፊ የመሬት ኢንቨስትመንት እንዲቆም ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይ ጫና እንዲያሣድሩ የሚጠይቅ ግልፅ ደብዳቤ ኦክላንድ ኢንስቲትዩት አውጥቷል፡፡

ካሊፎርኒያ የሚገኘው ይህ ኢንስቲትዩት ግልፅ ደብዳቤውን ያወጣው ነገ ግንቦት 11 ቀን 2004 ዓ.ም (በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር) በሜሪላንዷ ካምፕ ዴቪድ ከተጠራው የስምንቱ ከበርቴ ሃገሮች - ጂ8 ስብሰባ በፊት መሆኑ ነው፡፡

ለተጨማሪና ዝርዝር መረጃ ዘገባዎቹን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG