- የቻይናው ሺ ጂንፒንግ በጉባኤው አይገኙም
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚደረገው የቡድን 20 ሀገራት ጉባኤ ላይ ለመገኘት፣ ከሰዓታት በፊት ጉባኤውን በምታዘጋጀው ህንድ፣ ኒው ደሊ ከተማ ገብተዋል።
ፕሬዝደንት ባይደን ኒው ደሊ ሲደርሱ የህንዱ የመንገድ ትራንስፖርት እና የአውራ ጎዳናዎች ሚኒስትር ዴ’ታ፣ ቪጄይ ሲንግ፤ እንዲሁም በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጸሃፊ የሆኑት ቫኒ ራኦ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በዋና ዓባላቱ መካከል ክፍፍል እንዳለ የሚነገርለት የቡድን 20 ጉባኤ ላይ፣ የቻይናው ሺ ጂንፒንግ አለመገኘታቸው፣ የቡድኑን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ከቷል ሲል ኤኤፍፒ በዘገባው አመልክቷል።
ቡድን 20 የተባለው ስብስብ በቅድሚያ በእ.አ.አ 1999 ቡድን 7 በሚል ተመሥርቶ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ በነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት የዓለምን ኢኮኖሚ በተመለከተ ተቀራርቦ ለመነጋገር በሚል የተቋቋመ ነው። ከ 2008 ጀምሮ በየዓመቱ ጉባኤውን ሲያካሂድ ቆይቷል። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግን በዓባላቱ መካከል በተለያዩ የዓለም ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል።
አዘጋጇ ህንድ በመጨረሻ ሰዓት ላይም ጭምር የዩክሬኑን ጦርነትና የአየር ንብረትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ስምምነት እንዲኖር ስትሯሯጥ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ በዓባላቱ መካከል ያለው መፋተግ ግጭትን የሚጭር እና የሕዝብን አመኔታ የሚያሳጣ ነው ሲሉ ትናንት ተናግረዋል።
የቻይናው ፕሬዝደንት ሺ ጂንፒንግ በጉባኤው ላለመታደም ወስነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው የሆኑትን ሊ ቻንግ ወደ ኒው ደሊ ልከዋል።
መድረክ / ፎረም