አዲሱ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍራንሷ ባይሩ ሀገራቸው በአያሌ ችግሮች እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ሳምንት አዲሱን ካቢኔያቸውን ያቋቁማሉ፡፡የሽግግር በጀት እንዲመደብ የቀረበው ረቂቅ ህግ እንዲጸድቅ ግፊት ያደርጋሉ፡፡ ሀገሪቱን ከገባችበትን የበጀት አረንቋ ለማውጣት የሚያግዝ የረዥም ጊዜ በጀት ለሚመድበው ሕግ ድጋፍ ለማሰባሰብ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ከሳቸው በፊት ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ውድቀት ምክንያት ይህ እንደመሆኑ ፈታኝ እንደሚሆንባቸው ተመልክቷል፡፡
የ73 ዓመቱ አንጋፋ ፖለቲከኛ በደቡብ ምዕራብ ፓው ከተማ የረዥም ጊዜ ከንቲባ የነበሩ እና ለዘብተኛ አቋም ያላቸው ሲሆኑ በርካታ ሥራዎች እና ፈተናዎች ይጠብቋቸዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮን የሾሟቸው ፍራንሷ ባይሩ በዚህ ዓመት የተሾሙ አራተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው ፡፡ ባይሩ እጅግ የተከፋፈለ በሆነው የሕግ መምሪያው ምክር ቤት የኃይለኞቹ ግራ እና ቀኝ ዘመም ጎራዎች ከባድ ጭቅጭቅ ይጠብቃቸዋል፡፡
ባለፉት ወራት ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የግብርና ምርቶች፣ በሠራተኛ ጉዳዮች እና በሌሎችም ችግሮች ቅሬታ ለማሰማት አርሶ አደሮች፣ መምህራን፣ የሆስፒታል እና የባቡር ሠራተኞች ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አደባባይ ወጥተዋል።
የፈረንሳይ አለመረጋጋት አስቀድሞም ሩስያ ዩክሬን ውስጥ እያስመዘገበችው ባለው ድል እንዲሁም ከመጭው የትረምፕ አስተዳደር ጋር ተያይዞ በአትላንቲክ ተሻጋሪው ግንኙነት ላይ ሊከሰት በሚችለው መፈረካከስ ስጋት ላይ ያለውን የአውሮፓ ሕብረትን አሳስቦታል፡፡
ታዋቂው የፈረንሳይ ለ ሞንድ ጋዜጣ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ባይሩ “ከሌሎቹ ለረዘመ ጊዜ እንደሚቆዩ ወይም የተሻለ ስኬት እንደሚያገኙ የሚጠቁም ምንም ነገር የለም” ሲል በርዕሰ አንቀጹ አስነብቧል፡፡
መድረክ / ፎረም