በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፈረንሳይ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ያሏትን ወታደሮች ቁጥር ልትቀንስ ነው


የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን

ፕሬዚዳንት ዒማኑኤል ማክሮን፣ በአፍሪካ ያላቸውን ተሳትፎ ለመቀነስ ባላቸው ዕቅድ መሠረት፣ አገራቸው ፈረንሳይ፥ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ያሏትን ወታደሮች ወደ 600 ዝቅ ለማድረግ ማቀዷን፣ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

በአንዳንድ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች፣ የፀረ ፈረንሳይ ስሜት እየጨመረ በመምጣቱና እንደ ሩሲያ ያሉ ሀገራት የበለጠ ተጽእኖ ለመፍጠር ፉክክር ውስጥ በመግባታቸው፣ እ.አ.አ በ2023 የካቲት ወር፣ ማክሮን፥ የፈረንሳይ ወታደሮች በአፍሪካ የሚኖራቸውን ተሳትፎ “በከፍተኛ መጠን” እንደሚቀንሱ አስታውቀው ነበር።

ከአፍሪካ ጋራ ውይይት እየተደረገበት ባለው ዕቅድ መሠረት፣ ፈረንሳይ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸውን ኀይሎቿን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ማቀዷ ተመልክቷል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች እና አንድ ወታደራዊ ምንጭ፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት፥ ፈረንሳይ አሁን በመካከለኛው አፍሪካ በምትገኘው ጋቦን ያሏትን 350 ወታደሮች ወደ 100 ዝቅ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም፣ በምዕራብ አፍሪካዊቷ አይቮሪ ኮስት ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ከሚገኙት 600 ወታደሮቿ፣ 100 ብቻ ስታስቀር፣ በሰሜናዊ መካከለኛው አፍሪካ የምትገኘው ቻድ፣ አሁን ካሏት አንድ ሺሕ ወታደሮች ውስጥ 300 የሚጠጉትን ብቻ ታስቀራለች።

ፈረንሳይ፥ በማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር ወደ ሥልጣን በመጡ ወታደራዊ ኀይሎች ቀስ በቀስ እየተገፋች ወጥታለች፡፡ በአንጻሩ ሦስቱም ሀገራት፣ በአህጉሩ ላይ ተጽእኖዋን ለማስፋት ጥረት እያደረገች ከምትገኘው ሩሲያ ጋራ የጸጥታ ስምምነት አድርገዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG