የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማሕበረሰብ (ኢኮዋስ) ወታደራዊ መሪዎች ባለፈው ሳምንት በኒዠር በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ዙሪያ ናይጄሪያዋ ዋና ከተማ አቡጃ ላይ እየመከሩ ነው። በርካታ የአውሮፓ ሃገራት በአንጻሩ ዜጎቻቸውን ከኒዠር ማስወጣት ይዘዋል።
ኢኮዋስ ባወጣው አጭር መግለጫ የቡድኑ ወታደራዊ መሪዎች በኒዠር ሪፐብሊክ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ ዙሪያ ትኩረት የያዙት ምክክር እስከፊታችን አርብ ይዘቃል። በሌላ በኩል የኢኮዋስ የልዑካን ቡድን አባላት ከወታደራዊው ጁንታ አባላት ጋር ለመነጋገር ዛሬ ከዋና ከተማይቱ ገብተዋል።
የፈረንሳይ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ዜጎቻቸውን ከዚያች አገር በአውሮፕላን አጓጉዘው ለማውጣት በርካታ በረራዎችን አመቻችተዋል።
ፓሪስ ላይ ያረፉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት በረራዎች ከፈረንሳይ ዜጎች ሌላ የኒዠር፣ የፖርቱጋል፣ የቤልጂየም፣ የኢትዮጵያ፣ የሊባኖስ፣ የጀርመን፣ የካናዳ፣ የህንድ፣ የኦስትሪያ እና የዩናይትድ ስቴትስ ተወላጅ የሆኑ 350 ሰዎችን ማጓጓዛቸውን የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች እንደማትቀበል፤ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በመደገፍ፣ ሕጋዊ ሥርዓት እና የሰብአዊ መብቶች ይከበሩ ዘንድ ከኒዠር ሕዝብ፣ ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ)፣ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር እንደምትቆም በአንክሮ አስረድተዋል”
የጣሊያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ በበኩላቸው ኒዠርን ለቀው የወጡ ዜጎቻቸውን አሳፍሮ ዛሬ ረፋዱ ላይ ሮም ላይ የገባውን የጣሊያን አየር ኃይል አውሮፕላን የሚያሳይ ፎቶግራፍ አጋርተዋል።
ሮይተርስ አክሎ እንደዘገበው በበረራው 36 ጣሊያናውያን፣ 21 አሜሪካውያን፣ አራት ቡልጋሪያውያን፣ ሁለት አውስትራሊያውያን እና አንድ የብሪታንያ፣ አንድ የኒዥር፣ አንድ የሃንጋሪ፣ አንድ የሴኔጋል እና አንድ የናይጄሪያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች ተጓጉዘዋል።
ስፔይንም ዜጎቿን ከዚያች አገር ለማውጣት የበረራ ዕቅድ መያዟን አመልክታለች።
በሌላ ተያያዥ ዜና የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትላንት ማክሰኞ በወታደራዊ ጁንታው ከስልጣን ከተወገዱት የኒዠሩ ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙም ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።
ብሊንከን ለባዙም እና ለኒዠር ዲሞክራሲ “የማያወላውል ድጋፋቸውን” ገልጸዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
“ዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች እንደማትቀበል፤ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በመደገፍ፣ ሕጋዊ ሥርዓት እና የሰብአዊ መብቶች ይከበሩ ዘንድ ከኒዠር ሕዝብ፣ ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ)፣ ከአፍሪካ ኅብረት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር እንደምትቆም በአንክሮ አስረድተዋል” ብሏል።
ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ባደረጉት ሌላ የስልክ ጥሪ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን እና ሙሳ ፋኪ ማሃማት ባዙም በአስቸኳይ እንዲፈቱ በድጋሚ ጥሪ ማሰማታቸው ተዘግቧል።
መድረክ / ፎረም