በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፈረንሳይ ኮቪድ አስራ ዘጠኝን ለመግታት የሰዓት ዕላፊ አጸናች


በፈረንሳይ የኮሮና ቫይረስን መዛመት ለመቆጣጠር የታለመ የሰዓት ዕላፊ አዋጅ በተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎች ከዛሬ ጀምሮ በተወሰኑ አካባቢዎች ተግባራዊ ተደርጓል።

ዋና ከተማዋ ፓሪስ እና ሊዮን፥ ሞንፖሊዬ ፥ ሳንት ኢቲየንን ጨምሮ ቢያንስ በሰባት ከተሞች ከማታ ሶስት ሰዓት እስከንጋት አስራ ሁለት ሰዓት የሚዘልቅ የሰዓት ዕላፊ የታቀደ ሲሆን ለአራት ሳምንታት የሚቀጥል መሆኑ ተመልክቷል።

ቤልጂየምም በኮሮና ቫይረስ የሚያዘው ሰው ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ከፊታችን ሰኞ ጀምራ ከእኩለ ሌሊት እስከ ንጋት አስራ አንድ ሰዓት የሚዘልቅ የሰዓት ዕላፊ ተግባራዊ ልታደርግ ነው

ቤልጂየም ከዚህም በተጨማሪ ከሰኞ ጀምሮ የመጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች እንዲሁም ካፌዎች እንዲዘጉ ታዟል።

የዩናይትድ ስቴትስ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ እስራ ዘጠኝ መረጃ ማዕከል እንዳለው በዓለም ዙሪያ ያለው በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሰላሳ ዘጠኝ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ገብቷል፥ በበሽታው ምክንያት ህይወታቸውን ያጡት ደግሞ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ደርሰዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ ህንድ የኮቪድ አስራ ዘጠን መከላከያ ክትባት ሲገኝ በመጀመሪያ የሚከተቡትን ሶስት መቶ ሚሊዮን ሰዎች ለይታ የመመዝገብ ሂደት መጀመሯን ዘገባዎች አመለከቱ።

በህንድ የኮሮና ቫይረስ ተያዦች ቁጥር ማሻቀቡን ቀጥሏል፥ በአሃዙ ብዛት ዩናይትድ ስቴትስን ልትበልጥ እየተቃረበች መጥታለች።

ባሁኑ ወቅት በዩናይትድ ስቴትስ ያሉት የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ከስምንት ሚሊዮን አልፏል፥ ህንድ ደግሞ ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን ገብቷል።

ይህ በዚህ እንዳለ በዓለም ዙሪያ በየቀኑ የሚመዘገቡት የኮቪድ ተጋላጮች ቁጥር ከምንጊዜውም የገዘፈ ደረጃ ላይ ደርሷል፥ ይህ በተለይ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካና ላቲን አሜሪካ ሃገሮች ላይ እየታየ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አስረድቷል።

XS
SM
MD
LG